የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ በሩሲያና ዩክሬን ውጥረት ላይ ከፕሬዚዳንት ቭሎዶሚር ዘለንስኪ ጋር ለመምከር ዛሬ ማክሰኞ ወደ ዩክሬን ያመራሉ፡፡
ማክሮን ትናንት ሰኞ በተመሳሳይ ጉዳይ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር በሞስኮ ለሰዓታት ተነጋግረዋል፡፡
በሌላም በኩል የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት በሩሲያና ዩክሬን ውጥረት ላይ ለመምከር ከአዲሱ የጀርመን ቻንሰለር ጋር ትናንት ሰኞ በዋይት ኃውስ ተገናኝተዋል፡፡
Your browser doesn’t support HTML5
የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የሩስያውን ፕሬዚዳንት ካነጋገሩ በኋላ ለጋዜጠኞ በሰጡት አስተያየት አውሮፓ ከሩሲያ ጋር እንደ አውሮፓዊነት በህብረት አብራ ልትስራ የምትችልበትን መንገድ ማፈላለግ ያለባት መሆኑን እንዲህ በማለት አሳስበዋል፡፡
"በዚህ ጉዳይ ላይ ከፕሬዚዳንት ፑትን ጋርመግባባት የምንችል ይመስለኛል፡፡ ሩሲያ አውሮፓዊት ናት፡፡ በሩሲያዊነት የሚያምን፣ ከሩሲያ ጋር መስራት መቻልና፣ የወደፊቷ አውሮፓ፣ በአውሮፓውያን የምትገነባበትን መንገድ፣ መሻት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ይህ ቀላል ይሆናል? አይደለም፡፡ አውሮፓ ያለምንም እክልና ተግዳሮት በአፋጣኝ ልትገነባ ትችላለች ማለት ነው? አይደለም፡፡”
ፕሬዚዳንት ማክሮን ትናንት ሰኞ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ፑትን ጋር ሲነጋገሩ ብዙ አማራጭች የቀረቡ መሆኑን ቢጠቅሱም ዝርዝሩን ግን አልገለጹም፡፡
ሩሲያ ዩክሬንን ለመውረር ማቀዷን አስተባብላለች፡፡ ይሁን እንጂ ዩናይትድ ስቴትስና አጋርዎችዋ፣ ዩክሬንንና ሌሎቹ የቀድሞ የሶቭየት ህብረት አገሮች፣ የኔቶን አባል እንዳይቀላቀሉ ጠይቃለች፡፡ ወደ እነዚህ አገሮች የሚደረገውን የመሳሪያ ጓዝ እንዲቀንሱና ፣ የኔቶን ጦር ወደ ምስራቅ አውሮፓ ያደረገውን መስፋፋት እንዲቀለብስ ትፈልጋለች፡፡
በሌላም በኩል የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት እና የአዲሱ የጀርመን ቻንሰለር ኦላፍ ስኮሎዝ መላውን አውሮፓ ሊነካ በሚችለው የሩሲያና ዩክሬን ፍጥጫ ላይ ለመምክር ትናንት ሰኞ በዋይት ሀውስ ተገናኝተው መክረዋል፡፡ ሁለቱ መሪዎች በአካል ተገናኝተው ሲነጋገሩ ይህ የመጀመያቸው ነው፡፡ከንግግራቸው በኋላ ሩሲያ ዩክሬንን ብትወር ከፍተኛ ማዕቀብ ሊጠብቃት እንደሚገባ ሙሉ ስምምነት ያላቸው መሆኑን ፕሬዚዳንት ባይደን ተናግረዋል፡፡
የሩሲያን ጥያቄ አስመልክቶ ፕሬዚዳንት ባይደን በሰጡት ምላሽ ይህ ዩክሬንን የኔቶ አባል የማድረግና ያላማድረጉ ውሳኔ የራሷ የዩክሬን ምርጫ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ባለፈው እሁድም ወደ 1ሺ700 የሚደርሱ ልዩ ሥልጠና ያላቸው የአሜሪካ ወታደሮች ከዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ወደ ሚገኘው ደቡብ ፖላንድ ግዛት ደርሰዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ባይደን የዲፕሎማሲው መፍትሄው አሁንም የሚቻል መሆኑን ጠቅሰው የኔቶ ህብረት አገሮች ወታደራዊ መፍትሄን እንደ መጀመሪያው አማራጭ የማይመለከቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከጀርመኑን ቻንሰለርም ጋር የተነጋገሩት ይህኑን መሆኑን እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል
“በዛሬው እለት የጀርመን ቻንሰለር እና እኔ ስለ ጋራ ትብብራችን ተነጋግረናል፡፡ ሩሲያ የዩክሬንን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ብትጥስ፣ ፈጣን የሆነ ዓለም አቀፋዊ ማዕቀብና ጉዳት እንደሚጠብቃት በግልጽ የሚያሳይ ውሳኔ ላይ ተነጋግረናል፡፡ ጀርመንና በምስራቅ አውሮፓ ያሉ ሁሉንም አጋሮቻችንን፣ እንዲሁም የአውሮፓ ህብረትን በዚህ ዙሪያ በህብረት በመስራት ላደርጉት ጥረት ምስጋናዬን ላቀርብ እፈልጋለሁ፡፡ ሩሲያ ከዚህ አልፋ ሌላ ወረራ ብትፈጽም ነገሮች እንደሌላው ጊዜ ሊሆኑ እንዳማይችሉ ሁላችንም ተስማተናል፡፡
የጀርመን ቻንሰር ኦላፍ ባይደን ባሉት ነገር ሁሉ ተስማምተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከሩሲያ ወደ ጀርመን ስለተዘረጋው ትልቁ የኖርድ ስትሪም 2 የጋዝ መስመር ምንም የሰጡት ማረጋገጫ የለም፡፡ ገና ሥራ ያልጀመረው የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር በየዓመቱ 55 ቢሊዮን ኪዩቢክ የሚሆን የተፈጥሮ ጋዝ ከሩሲያ ወደ አውሮፓ እንዲያጓጓዝ የታቀደ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው፡፡ የጀርመኑ ቻንሰር ኦላፍ እንዲህ አሉ
“ለአሜሪካውያን ወዳጆቻችን የምንለው ነገር በአንድነት ተባብረናል፡፡ የምንወስደው እርምጃ አንድ ላይ ነው፡፡ አስለፈላጊውንም እርምጃ ሁሉ እንወስዳለን፡፡
ፕሬዚዳንት ባይደንም በኩላቸው ይህን ተናገሩ
“ሩሲያ ዩክሬንን ብትወር ያ ማለት ታንኮች ወታደሮች በድጋሚ የዩክሬንን ድንበር አቋረጡ ማለት ነው፡፡ ያ ከሆነ በኋላ ደግሞ የኖርድ ስትሪም 2 የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ ከዚያ በኋላ እንዲያበቃ እናደርገዋለን፡፡
የቀድሞዋ የጀርመን ቻንሰለር አንጀላ መርኬል የኖርድ ስትሪም 2 የጋዝ መተላለፊያ መስመሩን አስመልከቶ ከፕሬዚዳንት ባይደን ጋር ያላቸውን ልዩነት የሚያሰሙት በግልጽ ነበር፡፡ የአሁኑ አዲሱ የጀርመን ቻንሰለር የቀድሞዋን ቻንሰለር አቋም ሊከተሉ የሚችሉ መሆኑን ቢገመትም ከዚህ አቋም ትንሽ ዝንፍ ሊሉ እንደሚችሉ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ በአሜሪካ የጀርመን ጥናት ተቋም ጄፍሪ ራቴክ እንዲህ ይላሉ
“ይህ ግንኙነት ከጋዝ መስመሩ በላይ ከፍ ያለ ነው፡፡ ልዩነቱ እየጠበበ ነው፡፡ ምክንያቱም የጀርመን መንግሥት በእርግጥም ራሳቸው ቻንስለር ስኮሎዝ ሩሲያ በዩክሬን ላይ በምታካሂደው ጠብ አጫሪነት የኖርድ ስትሪም 2 የጋዝ መስመር ራሱ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ የሚችል መሆኑን አምነዋል፡፡”
ይሁን እንጂ በዚህ ፍጥጫ ሊደርስ የሚችለውም ጫና መሸከም ከባድ ለሚሆንባቸው ሁሉ የሚደርሰውን ጉዳት መሸከም ቀላል አይሆንላቸውም፡፡