Your browser doesn’t support HTML5
ከዐዲስ አበባ ወደ ደሴ እንዲሁም ከዐዲስ አበባ ወደ ጎጃም እና ጎንደር መሥመሮች የሚደረገው የየብስ ትራንስፖርት ስምሪት፣ ካለፈው ሳምንት አጋማሽ አንሥቶ መቋረጡን፣ የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሠሪዎች ፌደሬሽን አስታውቋል፡፡
የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኔ ዘሩ፣ ትላንት ሰኞ ለአሜሪካ ድምፅ ሲናገሩ፣ ለትራንስፖርት አገልግሎቱ መቋረጥ ምክንያቱ “ወቅታዊው የጸጥታ ችግር ነው፤” ብለዋል፡፡ ኃላፊው አክለው እንዳስረዱት ከዐዲስ አበባ ወደ ደሴ በሚወስደው መንገድ ስምሪቱ የተቋረጠው፣ ከቅዳሜ ጀምሮ ሲሆን፤ የጎጃም እና የጎንደር መሥመር ስምሪት በአንጻሩ ካለፈው ሳምንት ረቡዕ አንስቶ ነው።
መንገድ በመዘጋቱ፣ ለአንድ ሳምንት ያህል በመንገድ ላይ እንደቆሙ መኾናቸውን የገለጹት ያነጋገርናቸው የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች፣ ከምሥራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ከተማ አንሥቶ ባሉት የተለያዩ ከተሞች፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተሽከርካሪዎች ጉዟቸው መስተጓጎሉን ተናግረዋል፡፡
በዐማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የፋኖ አደረጃጀቶች የአንዱ አመራር አባል፣ በድርጅታቸው የተጠራ የመንገድ መዘጋት መኖሩን ዋሽንግተን ዲሲ ለሚገኙ የአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢዎች አረጋግጠዋል፡፡ ከመንግሥት በኩል አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፡፡