ወላጆች በግል ትምህርት ቤቶች የክፍያ ጭማሬ ምሬታቸውን እየገለጹ ነው

Your browser doesn’t support HTML5

ወላጆች በግል ትምህርት ቤቶች የክፍያ ጭማሬ ምሬታቸውን እየገለጹ ነው

በዐዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች፣ ለመጪው ዓመት የትምህርት ቤት ክፍያ፣ ከ20 እስከ 100 በመቶ የሚደርስ ጭማሬ ለማድረግ ማቀዳቸውን ይፋ አድርገዋል። በርካታ ወላጆች፣ “የኑሮውን ኹኔታ ያላገናዘበ ነው” ሲሉ የጠሩትን ጭማሬ ሲቃወሙ፣ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባና ያለአግባብ የታቀደውን ክፍያ እንዲያስቆም ጠይቀዋል።

በዐዲስ አበባ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች፣ የወርኀዊ ክፍያ ጭማሬ ዕቅዳቸውን ማቅረብ የጀመሩት፣ በሚያዝያ ወር ላይ ነው። በርካታ ወላጆች ግን ዕቅዱን ተቃውመዋል። የዐዲስ አበባ ከተማ የትምህርት እና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን በበኩሉ፣ ከወላጆች ጋራ በቂ ውይይት ሳይደረግ፣ የጭማሬ ዕቅዱን መተግበር እንደማይቻል በማሳሰቡ፣ ትምህርት ቤቶቹ ከወላጆች ጋራ የተለያዩ ስብሰባዎችን ሲያካሒዱ ቆይተዋል።

ወላጆች ከየትምህርት ቤቶቹ አመራሮች ጋራ ባካሔዷቸው ስብሰባዎች፣ አንዳንድ የተጋነኑ ጭማሬዎች በተወሰነ መልኩ እንዲቀንሱ ቢያግዝም፣ አጥጋቢ ስምምነት ላይ ለመድረስ አለማስቻሉን ወላጆች በምሬት ይገልጻሉ።

ሦስት ልጆቻቸውን ፊውቸር ታለንት አካዳሚ በተሰኘው ትምህርት ቤት የሚያስተምሩትና በመጪው ዓመትም አራተኛ ልጃቸውን ትምህርት ለማስጀመር መዘጋጀታቸውን የገለጹልን አቶ ለታሪክ ብሩ፣ ትምህርት ቤቱ በተማሪዎች ክፍያ ላይ 75 በመቶ ለመጨመር ዐቅዶ እንደነበር አውስተው፣ ከወላጆች ጋራ በተደረገው ውይይት፣ ጭማሬው፥ ከ20 እስከ 30 በመቶ እንዲኾን መስማማታቸውን ያስረዳሉ።

የዋና መዲናዪቱ የትምህርት ቢሮ ተወካዮች በተገኙበት፣ ወላጆች ያቀረቡት የማሻሻያ ሐሳብ ግን፣ በትምህርት ቤቱ ተቀባይነትን አላገኘም። ወላጆች በመጪው ዓመት፣ በተማሪዎች ክፍያ ላይ 55 በመቶ ጭማሬ እንዲያደርጉ ትምህርት ቤቱ አስታውቋል። በፊውቸር ታለንት ትምህርት ቤት፣ የወላጅ ኅብረት ኮሚቴ ውስጥ ለአምስት አመት ማገልገላቸውን የሚገልጹት አቶ ለታሪክ፣ ጭማሬው፣ ከወላጆች ዐቅም በላይ ነው፤ ይላሉ።

የከባድ መኪና አሽከርካሪ የነበሩትና አሁን በግል ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ተሾመ ገብረየስም፣ ሁለት የ9ኛ እና የ10ኛ ክፍሎች ተማሪዎች ልጆቻቸውን፣ በዚኹ ፊውቸር ታለንት ትምህርት ቤት ያስተምራሉ። እስከ አሁን በነበረው ተመን፣ በተርም(በሁለት ወር ከዐሥራ አምስት ቀን) 10ሺሕ 24 ብር ሲከፍሉ ቢቆይም፣በትምህርት ቤቱ ዕቅድ የተወሰነው 55 በመቶ ጭማሬ ግን፣ የወላጆችን ዐቅም ያገናዘበ አለመኾኑን በምሬት ያስረዳሉ።

በዐዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ 1ሺሕ558 የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ፣ 1ሺሕ 257 የሚኾኑቱ፣ በመጪው ዓመት የትምህርት ዘመን የክፍያ ጭማሬ ለማድረግ ማቀዳቸውን፣ የዐዲስ አበባ የትምህርት እና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን

አስታውቋል። ለጭማሬው በመነሻነት የሚያቀርቡትም፥ የቤት ኪራይ፣ የወረቀት እና የመሳሰሉት ግብዓቶች ዋጋ መናርንና የመምህራን ደመወዝ ጭማሬን ናቸው።

አቶ ለታሪክ እንደሚያስረዱት ግን፣ ከፍተኛ ጭማሬ እያደረጉ ካሉት ትምህርት ቤቶች አንዳንዶቹ፣ የራሳቸው ሕንፃ ያላቸው ጭምር በመኾናቸው፣ የተጠቀሱት ምክንያቶች ተቀባይነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ በታቀደው የክፍያ ጭማሬ፣ የመምህራን ደመወዝ ማሻሻያው፣ እዚኽ ግባ የሚባል እንዳልኾነ አመልክተዋል።

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ኢትዮ-ብሔራዊ ትምህርት ቤት፣ ያቀደውን የ30 በመቶ ጭማሬ አስመልክቶ፣ ከወላጆች ጋራ ሁለት ጊዜ ስብሰባ ቢያካሒድም ያለስምምነት ተበትኗል። ኾኖም፣ ባለፈው ሳምንት ለወላጆች በላከው የውሳኔ ደብዳቤ፣ በመጪው ዓመት ወላጆች አሁን በሚከፍሉት ክፍያ ላይ 30 በመቶ እንደሚጨምሩ በመግለጽ፣ ዕቅዱን ማጽናቱን አሳውቋል።

የስድስተኛ፣ የሰባተኛ እና የስምንተኛ ክፍል ልጆቻቸውን በትምህርት ቤቱ የሚያስተምሩት ወይዘሮ ትዕግሥት ተስፋዬ፣ እጅግ ከባድ ውሳኔ ከፊታቸው እንደሚጠብቃቸው በኀዘን ገልጸውልናል።

ኢትዮ-ብሔራዊ ትምህርት ቤት፣ በክፍለ ከተማው ካሉ ትምህርት ቤቶች የተሻለ ጥራት ያለውና በትምህርት አሰጣጡም የተመሰገነ ነው፤”

“ኢትዮ-ብሔራዊ ትምህርት ቤት፣ በክፍለ ከተማው ካሉ ትምህርት ቤቶች የተሻለ ጥራት ያለውና በትምህርት አሰጣጡም የተመሰገነ ነው፤” የሚሉት ወይዘሮ ትዕግሥት፣ ወላጆች የተለየ የገቢ ጭማሬ ባላገኙበትና የኑሮ ውድነቱ ከፍተኛ ጫና በፈጠረበት በአሁኑ ወቅት፣ ትምህርት ቤቱ የወሰነው የክፍያ ጭማሬ፣ በርካታ የማኅበረሰቡን አባላት እንዳስቆጣ ተናግረዋል።

የዐዲስ አበባ ትምህርት እና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ የግል ትምህርት ቤቶቹ እያሳለፉ ባሉት ውሳኔ ዙሪያ ምን አስተያየት እንዳለው ለመጠየቅ በተደጋጋሚ ብንሞክርም ምላሽ አላገኘንም። ኾኖም፣ ወላጆች ከመንግሥት ምን ይጠብቃሉ? ስንል የጠየቅናቸው ወይዘሮ ትዕግሥት፣ “አሁንማ ረፍዷል” የሚል፣ በቅሬታ እና ቀቢጸ ተስፋ የተመላ ምላሽ ነው የሰጡን።

በሌላ በኩል፣ የክፍያ ጭማሬ እንደሚያደርጉ ካሳወቁ ትምህርት ቤቶች ውስጥ፣ 1ሺሕ31 የሚኾኑቱ፣ ከወላጆች ጋራ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡ ከእነዚኽ ትምህርት ቤቶች አብዛኞቹ፣ ከ20 እስከ 60 በመቶ ጭማሬ ለማድረግ ከወላጆች ጋራ መስማማታቸውን አመልክቷል። ጭማሬውን መክፈል የሚችሉ ወላጆች፣ ልጆቻቸውን በትምህርት ቤቶቹ እያስተማሩ ሲቀጥሉ፣ ያልቻሉቱ ደግሞ፣ ልጆቻቸውን፥ ዐቅማቸው ወደሚፈቅድበት ትምህርት ቤት እንዲያዛውሩ ነው የተነገራቸው።