ጡረተኛዋ በጎ አድራጊ

Your browser doesn’t support HTML5

ጡረተኛዋ በጎ አድራጊ

በልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና በብዙ አገሮች ተዘዋውረው ለ42 ዓመት አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት፣ ማረፊያቸውን በአገራቸው በኢትዮጵያ አድርገው፣ በቂ ዐቅም የሌላቸው ሴት ተማሪዎች የሚማሩበት ኮሌጅ ከፍተዋል፡ የተላላፊ በሽታዎች ስፔሻሊስት ዶ/ር ትዕግሥት ግርማ፡፡

ዶ/ር ትዕግሥት፣ “ለደግ ሚድዋይፍሪ ኮሌጅ” የተሰኘውን ማኅበራዊ ድርጅት ያቋቋሙት በጡረታ ገንዘባቸው ነው።

አዲስ አበባ ውስጥ በቤተ ሰዎቻቸው ቦታ ላይ፣ ከአምስት ዓመት በፊት በአስገነቡት በዚኽ ኮሌጅ፣ ከወሊድ ጋራ በተያያዘ ከፍተኛ የሕክምና አገልግሎት ችግር ካለባቸው አካባቢዎች፣ ሴት ተማሪዎችን እየመለመሉ በማምጣት፣ ሙሉ ወጪያቸውን ሸፍነው በመጀመሪያ ዲግሪ ያሠለጥናሉ።

ተማሪዎቹ ሥልጠናቸውን ሲያጠናቅቁም፣ ተመልሰው የመጡበትን ማኅበረሰብ እንዲያገለግሉ ያደርጋሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት 115 ተማሪዎች ያሉት ኮሌጁ፣ ተማሪዎችን በኹለት ዙር አስመርቋል፡፡ ይህ፣ “የረዥም ጊዜ ሕልሜ ነው፤” ያሉት ዶ/ር ትዕግሥት፣ ለዚኽም የራሳቸው የውልደት ታሪክ መነሻ እንደኾናቸው ይናገራሉ፡፡ ለበጎ አድራጎት ሥራቸው፣ ከተለያዩ ተቋማት ዕውቅናና ሽልማት ያገኙት ገባሬ ሠናይትዋ፣ “ገንዘብ የማይገዛው ርካታ የሚሰጠኝ፣ ማኅበረሰቡ ተለውጦ ማየት ነው፤” ብለዋል፡፡

ከኮሌጁ ተማሪዎች መካከል ከአፋር ክልል የመጣችው ፋጡማ አብዱ፣ “ሙሉ ወጪዬ ተሸፎኖ የመማር ዕድል ማግኘቴ ለኔ ትልቅ ነገር ነው፤ ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ ሳይማር ያስተማረኝን የአፋር ሕዝብ ማገልገል እፈልጋለሁ” ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡ ሌላዋ ከደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ኮሌጁን የተቀላቀለችው ተማሪ ሸጊቱ አስማማው ደግሞ፣ “በኮሌጁ ቆይታዋ ከመደበኛ ትምህርት ባለፈ የሴትነትን ብርታትና ጽናት በተመለከተም ልምድና እውቀት አግኝቻለሁ” ትላለች፡፡

“ሙሉ ወጪዬ ተሸፎኖ የመማር ዕድል ማግኘቴ ለኔ ትልቅ ነገር ነው፤ ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ ሳይማር ያስተማረኝን የአፋር ሕዝብ ማገልገል እፈልጋለሁ”

የዶ/ር ትዕግሥት የበጎ አድራጎት ስራና ጥንካሬ “እስካሁን የነበረኝን አመለካከት ቀይሮታል” የምትለው ሸጊቱ፣ በምትኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ ያለውን የአመለካከት መዛነፍ ለመቀየር እንደምትሠራም ገልጻለች፡፡ ከዶ/ር ትዕግስት ልምድ በመውሰድ በይቻላል መንፈስ “በሂደት ራሴም የበጎ አድራጎት ስራ መጀመር እፈልጋለሁ” በማለትም ራዕይዋን ተናግራለች፡፡

“ለደግ ሚድዋይፍሪ ኮሌጅ” ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የኮሌጁ ዲን ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት ዶ/ር ጥላሁን ቦጋለ በበኩላቸው፣ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ማገልገላቸውን ገልጸው “እዚህ እንድቆይ ያደረገኝ የዶ/ር ትዕግስት የሀገር ፍቅርና ለህዝበባቸው ያላቸው መቆርቆር ነው” ብለዋል፡፡

በዚህ ዙሪያ የተሰናዳውን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።