በላሊበላ ነዋሪዎች ከጦርነት ለማገገም እየታገሉ ነው

Your browser doesn’t support HTML5

በላሊበላ ነዋሪዎች ከጦርነት ለማገገም እየታገሉ ነው

በሰሜን ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበውና ከትግራይ ክልል ድምበር በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው ላሊበላ ከተማ ከጦርነቱ በፊት የበርካታ ቱሪስቶች መዳረሻ ነበር። በጦርነቱ ምክንያት ግን የተለያዩ አስተዳዳሪዎች በተፈራረቁባት ከተማ ከአለት ተፈልፍለው የተሰሩትን ቤተክርስቲያናት ለማየት ይደረግ የነበረው ጉብኝት አሁን ቆሟል። ሄነሪ ዊልኪንስ ከዚህ ሁኔታ ለማገገም የሚደረገውን ጥረት ቃኝቶ ከላሊበላ ያደረሰንን ዘገባ ነው።

በባዶ እጅ ተቆራርጠው የተሰሩት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በዚህ ስፍራ ከ900 ዓመታት በላይ እንደቆሙ ይገመታል። ባለፈው ዓመት ግን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ላሊበላ የውጊያ ሜዳ በመሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የወደፊት ዕጣ ፈንታው በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳስበው ግለፆ ነበር።

በጦርነቱ ወቅት ከተማዋ ቢያንስ አምስት ግዜ በተለያዩ እጆች ላይ ወድቃለች - በትግራይ ኃይሎች፣ በፌዴራል መንግሥቱ እና በአጋር ሚሊሺያዎች።

በየነ አባተ በላሊበላ የሚገኘው 'ቶፕ 12' የተሰኘ ሆቴል ዋና እንግዳ ተቀባይ ነው። የህወሓት ሀይሎች ከተማዋን ተቆጣጥረው በነበረበት ወቅት ሆቴሉ መዘፈፉንና ለተዋጊዎቹ እንደሆስፒታል ማገልገሉን ይናገራል። ሆቴሉ ተፀዳድቶ እንደገና ሥራ ከጀመረ ገና ሁለት ሳምንቱ ነው።

"ዋናው ችግር ለውሃ ኃይል ማመንጫው የሚሆነው የውሃ አቅርቦት ነው። መንገዱ እራሱ ገና ተሰርቶ አላላቀም። ሥራው በኮንትራት የተሰጠው ለቻይናዎች ነበር። ግን የህወሓት ወታደሮች ሁሉንም ማሽኖች ወሰደዋቸዋል። በዛ ምክንያት ጎብኚዎች ወደዚህ አይመጡም። ጥቂት ጎብኚዎች ብቻ ናቸው በአይውሮፕን የመጡት።"

በሆቴሉ የደረሰው ከዚህም ሊከፋ ይችል ነበር። ከአጠገቡ ያለውን ሆቴል የህወሓት ወታደሮች ከጠቆጣጠሩት በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) በመጠቀም ጥቃት እንዳደረሰበት ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በሆቴሉ ውስጥ ሲገባ መስኮቶቹ ፈራርሰዋል፣ የተሰባበሩ መስታወቶች እና ሌሎች ፍርስራሾችም መሬቱን ሸፍነዋል።

የከተማዋ ኢኮኖሚ በዋናነት ኢትዮጵያዋውያን በሚያደርጉት ሀይማኖታዊ ጉዞ እና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ቤተክርስቲያናቱን ለማየት በሚመጡ ቱሪስቶች ላይ የተመሰረተ ነው። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና ግጭቱ ተደማምረውባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የጎብኚዎች ቁጥር እንዲወርድ አድርጎታል።

አሁን ከተማዋ ከሁኔታው ለማገገም እየታገለች ነው። የኤሌክትሪክ አገልጎት የለም፣ የውሃ አቅርቦትም በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት ደርሶበታል።

ከላሊበላ ቤተክርስቲያናት ከአንደኛው ወጪ የመታሰቢያ እቃዎችን የሚሸጠው ድንቁ ፈንተ እንደሚለው ህወሓት ተቆጣጥሮ በነበረበት ወቅት መተዳደሪያ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነበር።

"ጦርነቱ የንግድ ሥራዬን ሙሉ ለሙሉ ነው ያቆመው። በግጭቱ ጊዜ ማንም የመታሰቢያ እቃዎችንም ሆነ የሀይማኖት መፅሃፍትን ገበያ ወስዶ ለመሸጥ አይደፍርም ነበር፣ ምክንያቱ በጣም ስለሚፈሩ። ደግሞም የህወሓት ወታደሮች ያለን ገንዘብ በሙሉ ይወስዱብናል። ስለዚህ ዞር ብለን ለመቆየት ወሰንን።"

ሌላው በአካባቢው አስጎብኚ ሆኖ የሚሰራው አያሌው አብይ እንደሚለውም በግጭቱ ወቅት የንግድ ሥራው ሙሉ ለሙሉ ተዘግቶ የነበረ ሲሆን አሁንም ከሁኔታው ለማገገም የማይቻል ሆኖበታል።

"ይሄ ከመከሰቱ በፊት፣ በየሁለት ወይ በየሦስት ቀኑ የማስጎብኘት ስራ እሰራለሁ። ላለፉት ሦስት ዓመታት ግን ምንም ነገር አልነበረም። ሁሉም ነገር ተዘግቷል ወይ ታግዷል። እዚህ ማንም በትክክል ስራ እየሰራ ያለ የለም።"

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም የሆነው ዩኔስኮ ውስጥ የሚሰሩት ላዛሬ ኤሉንዶአሶሞ እንደሚሉት ተቋሙ ላሊበላን ለመደገፍ እቅድ አለው።

"ዋናው የሚያሳስበን ነገር በአካባቢው የሚኖሩት ማህበረሰብ ናቸው። ስለስፍራው የሚጨነቁ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ ለሆነው ታሪካዊ ቅርስ የሚያስቡ ማህበረሰብ ናቸው። ስፍራውን ተንከባክበው ለበርካታ ዘመናት ሲጠቀቡበት እንደቆዩት አሁንም እንዲጠቀሙበት ይፈልጋሉ።"

የዩኔስኮ ተወካዮች በዚህ ወር መጨረሻ ወደ ላሊበላ ተጉዘው ስፍራውን የመጎብኘትና ምን አይነት ድጋፍ እንደሚፈልግ የመገምገም እቅድ እንዳላቸው አሶሞ ተናግረዋል።