ቱርክ እና ሦሪያ ውስጥ በርዕደ መሬቱ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ17000 አለፈ

  • ቪኦኤ ዜና

ባለፈው ሰኞ ቱርክ እና ሦሪያ ውስጥ በደረሰው ከባድ ርዕደ መሬት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ17 ሺህ ማለፉ ተዘግቧል፡፡

ባለፈው ሰኞ ቱርክ እና ሦሪያ ውስጥ በደረሰው ከባድ ርዕደ መሬት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ17 ሺህ ማለፉ ተዘግቧል፡፡ በሁለቱም ሀገሮች የዕርዳታ ሰራተኞች ከፈራርሱት ህንጻዎች ስር በህይወት ተቀብረው ላሉ ሰዎች ለመድረስ ትናንት ሲሯሯጡ ውለዋል፡፡

ሰራተኞቹ ለዕርዳታ ርብርቡ የሚያስፈልጋቸው በቂ መሣሪያ እንደሌላቸው ተዘግቧል፡፡ የቱርክ የአደጋ ጊዜ ሥራ አመራር መስሪያ ቤት ትናንት በሰጠው መግለጫ የመሬት ነውጡን ሰለባዎች ለመፈለግ በተያዘው ጥረት ወደ 110 ሺህ የሚሆኑ ሰራተኞች እንደተሰማሩ አመልክቷል፡፡

5500 ትራክተሮች፡ አፈር ገልባጮች፡ መቆፈሪያዎች እና ክሬኖችን ጨምሮ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች ወደሀገሪቱ ተልከዋል፡፡

የቱርክ ፕሬዚደንት ሬቼፕ ታይፕ ኤርዶዋን የመሬት ነውጡ የተቀሰቀሰበት ቦታ አጠገብ ያለች ከተማን እና የቱርክ እና ሦሪያ ድንበር አካባቢን ጎብኝተዋል፡፡ የጠፉባቸውን ቤተሰቦቻቸውን ፍለጋ ላይ ያሉ ቤተሰቦች እና መንግሥት ዕርዳታ እንዲሰጥ የጠየቁ ሰዎች ብሶታቸውን የገለጹላቸው ሲሆን ፕሬዚዳንቱ መንግሥት በምላሽ አሰጣጡ በኩል ችግሮች እንዳሉት አምነዋል፡፡

“እንዲህ ላለ አደጋ መዘጋጀት አይቻልም” ያሉት ፕሬዚዳንቱ “አንድም የምንተወው ሰው የለም ፡ ለዜጎቻችን በሙሉ እንደርሳለን” ብለዋል፡፡

ወቅቱ ክረምት መሆኑን እና የአውሮፕላን ማረፊያው በርዕደ መሬቱ መውደሙ የእርዳታ ሥራዉን እንዳስተጓጎለ አስረድተዋል፡፡

የዕርዳታ ሰራተኞች አሁንም በፍርስራሹ ውስጥ በህይወት ያሉ ሰዎችን እያገኙ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ሰዎቹን ከተቀበሩበት ለማውጣት የሚያስፈልገው መሳሪያ እና ዕውቀቱ ስለሌላቸው የድረሱልን” ዋይታ ቢሰሙም ሊደርሱላቸው እንዳልቻሉ ይናገራሉ፡፡

የቱርክ ባለሥልጣናት እንዳሉት በርዕደ መሬቱ ከ14ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል፡፡ ከ63 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ቆስለዋል፡፡

በሶሪያ ደግሞ የሀገሪቱ መንግሥት እና የዕርዳታ ቡድኖች እንዳሉት ቢያንስ 3100 ሰዎች ሞተዋል፡፡

ሰኞ ዕለት በሁለቱ ሀገሮች የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ እአአ በ2011 ጃፓን ውስጥ ከ20ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ከገደለው የመሬት ነውጥ እና ሱናሚ ወዲህ ከደረሱት ሁሉ ከባዱ መሆኑ ተዘግቧል፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሦሪያ አስተባባሪ ትናንት ረቡዕ እንዳስታወቁት በሀገሪቱ በመሬት ነውጡ 10 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሰዎች ተጎድተዋል፡፡

ለዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት በተካሄደባት ሀገር በሦሪያ 15 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰብዓዊ ዕርዳታ ጠባቂዎች እንዳሉ ተመልክቷል፡፡