ስለ ተስፋ፣ ስለ አብዮት፣ ስለ ልጅነት፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ሕይወት .. ስለሌሎችም አያሌ ጉዳዮች ጽፏል፤ ገጥሟል፤ ተውኔት ደርሷል፤ በተዋናይነትም ተሳትፏል። በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ተነባቢነት ያተረፈ ታሪክ ቀመስ ልቦለድ መጽሐፍ ወደ አማርኛ መልሷል። ስዕል ለመሞከርም ጊዜ አላጣም። የመጽሔት እና የተነባቢ ጋዜጣ መራሄ አርታኢ ሆኖም ለረዥም ዓመታት አገልግሏል። በአጭሩም በሞከራቸው በርካታ የጥበብ ዘርፎች የተሳካለት ሁለገብ ከያኒ ነው - በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ዕውቅ ብዕረኛ ነቢይ መኰንን።
“ጥቁር ነጭ እና ግራጫ” እና “ስውር ስፌት - አንድ እና ሁለት” .. ለሕትመት የበቁ የግጥም መድብሎቹ ናቸው። ‘ናትናኤል ጠቢቡ’ እና ‘ጁሊየስ ቄሳር’ የተሰኙትን ተውኔቶች ተርጉሟል።
ወደር የሌለው ግሩም ተርጓሚም ነው”
የነቢይ ድርሰት በሆነው “ባለ ጉዳይ” በተሰኘው ተወዳጅ ተከታታይ የቴሌቭዥን ድራማ ዋናውን ገጸ ባሕሪ የተጫወተው አንጋፋው ተዋናይ አበበ ባልቻ ከተወዳጅ የሥነ ግጥም ሥራዎቹ እና ከተውኔት ድርሰቱ ባሻገር “ወደር የሌለው ግሩም ተርጓሚም ነው” ሲል ያወድሰዋል። ነቢይ በተጨማሪም ባለካባ እና ባለ ዳባ በተሰኘው ተውኔት ላይ በተዋናይነት ተሳትፏል።
እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1936 የተጻፈውን እና በአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት ዘመን በነበሩ ሁኔታዎች ላይ የሚያጠነጥነውን የአሜሪካዊቱን ሥመ ጥር ደራሲ ማርጋሬት ሚሼል’ን Gone with the Wind’ን ተርጉሞ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት ከፓለቲካ ጉዳይ ጋር በተያያዘ እስር ላይ በነበረበት በ1970ዎቹ በሲጋራ መጠቅለያ ቁርጥራጭ ወረቀት ላይ ጽፎ እያሾለከ በማውጣት ከእስር ከተለቀቀ በኋላ ‘ነገም ሌላ ቀን ነው’ በሚል ርዕስ አሳትሞ ለንባብ አብቅቷል።
ሦስት የሞያ አጋሮቹ እና ወዳጆቹ ህይወት እና ሥራውን ለመዘከር በተሰናዳ ውይይት የእርሱን በመሰለ ጨዋታ እና ቁም ነገር ያስታውሱታል።
Your browser doesn’t support HTML5