የራማፎሳ ቅሌት ምርመራ ሁለት ዓመት ሊወስድ ይችላል ተባለ

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል፦ ሰሪል ራማፎሳ

ከሁለት ዓመት በፊት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሰሪል ራማፎሳ የገጠር ቤት ውስጥ ዘራፊዎች መግባታቸውን ተከትሎ በተደረገ ምርመራ፣ 4 ሚሊዮን ዶላር የቤት ዕቃ ውስጥ ተደብቆ በመገኘቱ ጉዳይ ላይ የሚደረገው ምርመራ ሁለት ዓመት ሊወስድ እንደሚችል የሀገሪቱ እንባ ጠባቂ አስታውቀዋል።

ቅሌቱ ባለፈው ሰኔ ይፋ የሆነው የቀድሞው የሀገሪቱ የሥለላ ተቋም አለቃ በፕሬዚዳንቱ የገጠር ቤት አራት ሚሊዮን ዶላር ተደብቆ መገኘቱንና እንዲሁም ለዘረፋ የገቡትን ሰዎች በማሳፈን ምስጢር እንዳያወጡ ጎቦ ሰጥተዋል ብለው ለፖሊስ ሪፖርት ካደረጉ በኋላ ነው።

በሁለት ዓመት ውስጥ ምርመራውን ማጠናቀቅ እንደሚሹና ይህን የሚያደርጉትም የሃገሪቱን የፖለቲካ የግዜ ሰሌዳ ተከትለው እንዳልሆነ የእንባ ጠባቂ ተቋሙ ኃላፊ ኮሌካ ጋሌካ ተናግረዋል።

የእንባ ጠባቂ ተቋሙና ፖሊስ በ69 ዓመቱ ፕሬዚዳንት ላይ የቀረበውን በህገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ የማድረግ ውንጀላ በመመርመር ላይ ነው።

እንደ ኤኤፍፒ ዘገባ ከሆነ ተቋሙ ለፕሬዚዳንት ራማፎሳ 31 ጥያቄዎችን ልኮ በሁለት ሳምንት ውስጥ መልስ እንዲሰጡ ጠይቆ የነበረ ቢሆንም፣ ፕሬዚዳንቱ ቀኑ ይራዘምልኝ በማለታቸው ተጨማሪ ግዜ ተሰጥቷቸዋል።

የቀድሞ ነጋዴና የሠራተኛ ማኅበራት መሪ የሆኑት ራማፎሳ እአአ በ2018 ፕሬዚዳንትነቱን ወንበር ያገኙት፣ ከእርሳቸው በፊት ከነበሩትና የሥልጣን ዘመናቸው በሙስና ከጎደፈው ጃኮብ ዙማ ይልቅ ከሙስና ጋር ያልተነካኩ ሆነው እራሳቸውን በማቅረባቸው ነው ተብሏል።