የእንግሊዟ ንግሥት የነበሩት የዳግማዊት ኤልዛቤጥ የቀብር ሥነ ሥርዓት የዓለም መሪዎችና ነገሥታት በገኙበት በዌስት ሚኒስተር አቢ ዛሬ ተፈጽሟል።
ቀኑ የሃዘን ቢሆንም በከፍተኛና ደማቅ እንዲሁም ንጉሣዊ ሥርዓትና ወግን በተከተለ መንገድ ቀብሩ ተፈጽሟል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን ጨምሮ የሃገራት መሪዎች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮችና ነገሥታት በቀብሩ ላይ ተገኝተዋል።
ለ70 ዓመታት ዙፋን ላይ የቆዩት ንግሥት ኤልሳቤጥ ያረፉት ከ11 ቀናት በፊር በ96 ዓመታቸው ነበር።
ሌሎች ልጆቻቸውን ጨምሮ፣ አዲሱ ንጉሥ ቻርለስና ሁለት ልጆቻቸው ዊሊያምና ሃሪ፣ አስከሬኑን በእግራቸው በማጀብ ወደ ፍትሃት አዳራሹ አምርተው ከሌሎች የቤተሰቡ አባላት ጋር ተቀላቅለዋል።
“የተመለከትነውን ያህል ፍቅር ያገኙ መሪዎች በጣም ጥቂት ናቸው” ብለዋል የካንተበሪ ሊቀ ጳጳስ ጀስቲን ወልቢ ዛሬ ባሰሙት ስብከት። ንግሥቲቱ ብዙ ሰዎችን ያገለገሉት እግዚአብሄርን መሰረት አድርገው እንደነበርም መስክረዋል።
አዲሷ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትርና ግሥቲቱ ከመሞታቸው ሁለት ቀን በፊት ሹመታቸውን ለመቀበል በመኖሪያቸው ያገኟቸው ሊዝ ትረስ ትምህርታዊ ንግግራቸውን ወደ ሁለት ሺህ ለሚገመተው ታዳሚ አሰምተዋል።
ከሁለት ደቂቃ የህሊና ፀሎት በኋላ፣ ንጉሥ ቻርለስና ቤተሰባቸው አስከሬኑን አጅበው ወደ ዌሊንግተን አርች ካመሩ በኋላ፣ ግበዓተ መሬቱ ወደሚፈጸምበት ዊንዘር ካስል አምርተዋል።