የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ አንድ ከፍተኛ የቫግነር ቅጥር ወታደራዊ ቡድን አዛዥን፣ በዩክሬን “የበጎ ፈቃደኛ ተዋጊ ቡድኖችን” እንዲመሠርቱና እንዲመሩ አዘዋል።
የፑቲን ትዕዛዝ፣ የቅጥር ወታደራዊ ቡድኑ መሪ የነበሩት የቭጌኒ ፕሪጎዥን ከሞቱ በኋላ፣ ክሬምሊን ከቡድኑ ጋራ መሥራት እንደቀጠለች ያመለክታል፤ ተብሏል።
የአንድሬ ትሮሼቭ ሓላፊነት፣ ለውጊያ ዝግጁ የኾነ የበጎ ፈቃደኛ የእግረኛ ጦር ማቋቋም እንደኾነ፣ ፑቲን ተናግረዋል።
ዐዲሱ የፑቲን ትዕዛዝ፣ የቡድኑ መሪ ፕሪጎዥን፣ ባለፈው ሰኔ ወር በክሬምሊን ላይ ዐመፅ አሥነስተው፣ በነሐሴ ወር በአጠራጣሪ ኹኔታ ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ፣ ሞስኮ፣ የቫግነር ተዋጊዎችን መልሳ በዩክሬን ለማሰማራት ማቀዷን እንደሚያመለክት ተጠቁሟል።
የቫግነር ተዋጊዎች፣ በዩክሬን የባክሙትን ከተማ ከተቆጣጠሩ በኋላ ለቀው በመውጣት በሞስኮ ላይ የአጭር ጊዜ ዐመፅ ካሥነሱ በኋላ፣ ይህ ነው የሚባል የውጊያ ተሳትፎ አልነበራቸውም።