ፑቲን የሩሲያ ኒውክሌር ኃይሎችን የአጸፋ ልምድድ አስጀመሩ

ፎቶ ፋይል፦ የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለጠላት ጥቃት አፀፋዊ የኒውክሌር ጥቃት ምላሽ በመሰጠት ላይ ያተኮሩ መጠነ ሰፊ የኒውክሌር ኃይል ልምምዶችን ዛሬ ማከሰኞ አስጀመሩ።

ፑቲን ይህን ያስጀመረቱ ከወታደራዊ ባለስልጣናት ጋር በቪዲዮ በተደረገ ውይይት ነው፡፡ በውይይቱም ላይ ፑቲን ከፍተኛ ባለስልጣኖች የኒውክሌር ወንጫፊ የባለስቲክ እና ክሩዝ ሚሳይሎችን ጨምሮ የኒውክሌር መሣሪያዎችን በመጠቀም የሚወስዷቸውን ርምጃዎች ይለማመዳሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የመከላከያ ሚኒስትር አንድሬ ቤሎሶቭ “ልምምዱ ሩሲያ በጠላት የኒውክሌር ጥቃት ቢደርስባት የሩሲያ ስትራቴጂካዊ ጥቃት ኃይሎችን ለተቀናጀ የኒውክሌር ምላሽ ለማዘጋጀት ያለመ ነው፡” ብለዋል፡፡

ፑቲን የሩስያ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ለሀገሪቱ ሉዓላዊነት እና ለደህንነት ወሳኝ መሆኑን፣ በተለይም በዩክሬን ግጭት ምክንያት ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያለው ውጥረት እየተባባሰ መምጣቱን በመጥቀስ በዛሬ ማክሰኞው ንግግራቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

ምዕራባውያን ለዩክሬን ለሚያደርጉት ድጋፍ ፑቲን ቀደም ሲል በሰጡት ምላሽ “ዩክሬን በምዕራቡ ዓለም የተደገፈ የጦር መሣሪያ ተጠቅማ ሩሲያ ውስጥ ዘልቃ ገብታ እንድታጠቃ መፍቀድ ጦርነት እንደመጫር ይቆጠራል” ሲሉ ኔቶን አስጠንቅቀዋል።

ሩሲያ በዚህ ዓመት አንዳንድ የሩሲያ ስልታዊ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች የተሳተፉበትን ከቤላሩስ ጋር የተደረጉ የጋራ ልምምዶችን ጨምሮ ተመሳሳይ የሆኑ በርካታ የኒውክሌር ልምምዶችን አካሂዳለች፡፡