ፑቲን ቡድን 20 ጉባዔ ላይ አይገኙም

  • ቪኦኤ ዜና
ፎቶ ፋይል፦ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን

ፎቶ ፋይል፦ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን

የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ኢንዶኔዥያ ባሊ ላይ በሚካሄደው የቡድን 20 መሪዎች ጉባዔ ላይ እንደማይገኙ አስተናጋጇ ሀገር ኢንዶኔዥያ አረጋግጣለች፡፡ የበለጸገ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገሮች ሃያ ሀገሮች መሪዎች በአካል የሚገኙበት ጉባዔ የፊታችን ማክሰኞ እአአ ህዳር 15 ቀን ይከፈታል፡፡

ሞስኮን ወክለው የሚገኙት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ላቭሮቭ እንደሚሆኑ የኢንዶኔዥያ ማሪታይም እና መዋእለ ነዋይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለቪኦኤ ገልጸዋል፡፡ ፑቲን ከጉባዔው ስብሰባዎች በአንዱ ላይ በኢንተርኔት አማካይነት ሊሳተፉ ይችሉ ይሆናል ሲሉም ቃል አቀባዩ አክለዋል፡፡

ጃካርታ በዩክሬን ላይ የከፈተችውን ወረራ ለቀጠለችው ለሩሲያ መሪ በጉባኤው ላይ እንዲገኙ ያስተላለፈችላቸውን ግብዣ እንድትሰርዝ ምዕራብ ሀገሮች ወጥረው ስለያዟት ፑቲን ጉባዔው ላይ በርቀት በኢንተርኔት ቢካፈሉ ሊገላግላት ይችላል፡፡

ዲፕሎማሲያዊ ተጽዕኖውን ተቋቁመው የቆዩት የኢንዶኔዥያ ፕሬዚደንት ጆኮ ዊዶዶ የቡድን ሃያ አባል ያልሆነችውን የዩክሬንን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪንም ጉባዔው ላይ እንዲገኙ ጋብዘዋቸዋል፡፡

በኢንዶኔዥያ የዩክሬን አምባሳደር ቫሲል ሃሚያኒን ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ

“በርግጠኝነት ጉባኤው ላይ ይገኛሉ” ብለዋል፡፡ የሚገኙት በአካል ይሁን በርቀት በውል አልገለጹም፡፡