ለኢትዮጵያ ክሥ ግብፅ መልስ ሰጠች

ፎቶ ፋይል

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አለመረጋጋት ያለውን አለመረጋጋት “ያቀናጃሉ፥ ይመራሉ፥ ከጀርባ ድጋፍ ይሰጣሉ” ሲሉ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የሚወነጅሏቸው የሃገር ውስጥና የውጭ ኃይሎች ምላሾችን እየሰጡ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በሚካሄደው እንቅስቃሴ ሃገራቸው የትኛውንም ተቃዋሚ ደግፋ እንደማታውቅ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ ኤል-ሲስ አስታወቁ፡፡

ፕሬዚዳንት ኤል-ሲሲ ለአንድ የሀገራቸው ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ ሀገራቸው በኢትዮጵያ ላይ አንዳችም ሴራ እንደማትሸርብ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳነቱ በማከልም “ለኢትዮጵያዊያን ወንድሞቻችን ፓርላማቸው ፊት ቀርቤ በሰጠሁት ቃል እኛ ከግጭት ይልቅ መተባበርን መምረጣችንን እንደተናገርኩት ሁሉ ዛሬም ይህንኑ አረጋግጣለሁ” ብለዋል፤ በዚሁ ትናንት ሐሙስ በሰጡት መግለጫ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር - ኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ ዛሬ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል የኢትዮጵያ ችግር በራሱ በድርጅቱ ውስጥ የተፈጠረ መሆኑን ኢሕአዴግ እራሱ በቅርቡ ማመኑንና “ጣታችንን ወደ ሌላ ከመቀሰር እራሣችንን መቀየር አለብን፤ እራሣችን ነን በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያጣነው” ብሎ ተናግሮ እንደነበር አስታውሰው ኦነግ ከግብፅ መንግሥት ጋር የፈጠረው ምንም ግንኙነትና ያገኘውም እርዳታ እንደሌለ ገልፀዋል፡፡

የኦሮምያ ሚድያ ኔትወርክ የሚባለው መገናኛ ብዙኃን ሥራ አስኪያጅ አቶ ጃዋር መሐመድ በበኩሉ በእንቅስቃሴው ውስጥ የእርሱ ሚና እንደ አንድ የኦሮሞ ወጣት “ምክር መስጠት፣ ኦሮምያ ውስጥ የሚካሄዱ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣዎችን ማጋለጥና ለዓለም መገናኛ ብዙኃን ማሳወቅ” መሆኑን ጠቁሞ የኦሮሞ ሕዝብ ትግል በመሬት ባለቤትነት፣ በሰብዓዊ መብቶች አያያዝና በመሣሰሉ የሃገር ውስጥ ጉዳዮች ላይ የተመሠረተ መሆኑን አመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ሰሞኑን ለፓርላማቸው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ከኦነግና ከግንቦት ሰባት በተጨማሪ የግብፅ የመንግሥት ተቋማት ውጥረቱን በማባባስ መክሰሳቸው ይታወሣል፡፡

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡

Your browser doesn’t support HTML5

ለኢትዮጵያ ክሥ ግብፅ መልስ ሰጠች