በሺዎች የሚቆጠሩ የዩክሬን ህጻናት፣ ሩሲያ ወደተቆጣጠረቻቸው ግዛቶች መወሰዳቸውን የተቃወሙ ሰልፎች ባሳለፍነው ቅዳሜ እና እሁድ በዩናይትድ ስቴትስ የተለያዩ ከተሞች ተካሂደዋል።
በሲያትል የሚገኙ፣ በመቶ የሚቆጠሩ ዩክሬናውያን፣ “ልጆቻችን መልሱ” በሚል መሪ መፈክር፣ በበርካታ የአሜሪካ ከተሞች የተካሔደውን ሰልፍ ተቀላቅለዋል።
ልጆቻችንን መልሱ'
የዩክሬን ባለሥልጣናት እንደሚሉት፣ የሩሲያ ወረራ ከጀመረ አንሥቶ፣ 20 ሺሕ የሚደርሱ ሕፃናት፣ በሕገ ወጥ መንገድ ተወስደዋል፤ የተመለሱት ሕፃናት ቁጥር፣ ከ400 እንደማይበልጡም ተናግረዋል።
“ዛሬ፣ እዚኽ ሰማዩ እያለቀሰ ባለበት ወቅት፣ በዩክሬን የሚገኙ እናቶች እና አባቶች፣ ለልጆቻው እያለቀሱ ነው። አገራችንን ለማጥፋት በሚሹ፣ በሩሲያ ባሉ ሰዎች ነው ልጆቹ የተጠለፉት፡፡ ልጆችን እየጠለፉ እና ፕሮፓጋንዳ እየመገቡ ወደ ሩሲያዊነት ለመቀየር እየሞከሩ ነው፤ አልተሳካላቸውም፤” ብለዋል፣ የዩክሬን የክብር ቆንስላ የኾኑት ቫለሪ ግሎቦሮድኮ።
በዓለም አቀፉ የፍትሕ ችሎት፣ በመስኮብ ላይ የቀረበው ክሥ፣ ባለፈው ሳምንት መሰማት ጀምሯል። ሩሲያ እንደምትለው፣ ልጆቹ ከዩክሬን የተወሰዱት፥ ሰብአዊ መብታቸውን ለመጠበቅ እና በቤተሰቦቻቸውም ፈቃድ ነው።
አና ኪሪዬንኮ፣ ከአንድ ዓመት በፊት ወደ ዋሽንግተን ግዛት የመጣችው፣ ማሊን ከተሰኘች የዩክሬን ግዛት ነበር። “በርካታ ሕፃናት በሩሲያ ተወስደዋል። በርካቶቹ፣ የሥነ ልቡና ጉዳት ደርሶባቸዋል። በሰላም መተኛት አይችሉም፤” ብላለች አና።
Your browser doesn’t support HTML5
በዋሽንግተን ዲሲ በተደረገ ተመሳሳይ ሰልፍ ላይ፣ የቱርክ የመብት አቀንቃኝ ቸመን ኦር ለቪኦኤ የሩሲያ ቋንቋ አገልግሎት እንደተናገረችው፣ “ታሪክ ራሱን በዩክሬን በመድገም ላይ ነው።” አያይዛም፣ “ልጆቹ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እንሻለን። አገራቸው ዩክሬን ነው። እያንዳንዱ ሕፃን ወደ ወላጆቹ መመለስ አለበት። የገደሏቸው ሕፃናት ጉዳይ ግን ልብ የሚያደማ ነው። ኀዘን ይሰማናል፤” ስትል፣ ቸመር ተናግራለች።
በሎስ ኤንጀለስ በተደረገው ሰልፍ ላይ ደግሞ፣ ከኪየቭ የመጣችው ኢሪና ደምቺሺና፣ ለቪኦኤ የዩክሬን አገልግሎት እንደተናገረችው፣ አገሯን ለቃ የወጣችበት ዋና ምክንያት ለሴት ልጇ ደኅንነት ስትል ነው። “አንዳንድ ሰዎች ግን፣ ምን እየተካሔደ እንደኾነ እንኳን ምንም አያውቁም። ጦርነት እየተካሔደ ስለመኾኑም ከሰሙ፣ እንዲሁ በደምሳሳው እንጂ፣ በዩክሬን ስላለውና በሕዝባችን ላይ እየደረሰ ስላለው የሠቆቃ መጠን ምንም አያውቁም፤” ስትል ተደምጣለች ኢርና።
በሕገ ወጥ መንገድ፣ ሕፃናትን ከዩክሬን አውጥተው አግተዋል፤ በሚል፣ የዓለም አቀፉ ወንጀል ችሎት፣ በሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንና በአገሪቱ የሕፃናት መብት ኮሚሽነር ማሪያ ልቮቫ-ቤሎቫ ላይ፣ ባለፈው መጋቢት ወር የመያዣ ትዕዛዝ አውጥቶ ነበር።