ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ዛሬ፤ ሐምሌ 3/2013 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ውጤት መሠረት ድምፅ ከተሰጠባቸው 436 የምርጫ ክልሎች ገዥው ብልፅግና ፓርቲ 410ሩን አሸንፏል። በዚህም ብልፅግና ፓርቲ አዲስ መንግሥት በመመሥረት ኢትዮጵያን ለቀጣቹ 5 ዓመታት ለማስተዳደር የሚያስችለውን አብላጫ መቀመጫ በተወካዮች ምክር ቤቱ ውስጥ አግኝቷል።
ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው 410 መቀመጫ ከአጠቃላዩ የምክር ቤቱ 547 መቀመጫ ከ2/3ኛ በላይ መሆኑ ነው።
ተቃዋሚ ፓርቲዎች በድምሩ 13 መቀመጫዎችን ማሸነፋቸው የተገለፀ ሲሆን በሦስት የምርጫ ክልሎች ድጋሚ ቆጠራ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
ለክልል ምክር ቤቶችም ከጥቂቶቹ በስተቀር ብልፅግና ፓርቲ አብዛኛውን መቀመጫ ማሸነፉንና በተለያዩ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 10 የምርጫ ክልሎች ላይም ምርጫው በድጋሚ እንዲካሄድ መወሰኑን ቦርዱ አስታውቋል።
የምርጫ ቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ባደረጉት ንግግር ቦርዱ ተዓማኒ ምርጫ ማድረጉን ተናግረዋል።
ውጤቱ ይፋ በተደረገበት ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ለአሸናፊው ፓርቲ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈው ተፎካካሪዎች ቅሬታ ካላቸው በሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።
ለቦርዱ የተለያዩ ድጋፎችን ካደረጉ አካላት መካከል አንዱ የሆነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምርጫው ሂደት ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ ለቦርዱ ድጋፉን እንደሚቀጥል ገልጿል።
ጀርመንም ለቦርዱ ድጋፍ ካደረጉ ወገኖች አንዷ ስትሆን ኢትዮጵያ ያሉት አምባሳደሯ በቀጣይነት በትግራይ ክልልም ምርጫ ማድረግ እንደሚቻል ያላቸውን ተስፋ ገልፀው ለዚህም የክልሉ ሰላም እንዲረጋገጥ ችግሮች በፖለቲካዊ መንገድ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፓርቲያቸው ብልፅግና በ 6ኛው አገራዊ ምርጫ ማሸነፉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ምርጫውን “በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ከተፅዕኖዎች በተላቀቀ የምርጫ ቦርድ ዳኝነት የተደረገ” ብለውታል።
“ፓርቲያችን በሕዝብ ይሁንታ አግኝቶ ሀገር ለማስተዳደር መመረጡ አስደስቶናል - ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ - በውጤቱም ከአሸናፊነት ይልቅ ኃላፊነት፣ ከድል አድራጊነት ይልቅ ታላቅ የሆነ ሀገራዊ አደራ እንዲያድርብን አድርጎናል” ብለዋል።
ጠቅላም ሚኒስትሩ አክለውም “ተፎካካሪ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸውም እስከሚቀጥለው ምርጫ በመንግሥት አስተዳደርና ሕዝብን በማገልገል ሂደት ውስጥ ሚናቸው ሰፊ ሊሆን እንደሚገባ ለማስታወስ እወዳለሁ” ብለዋል።
“በቀጣይ ወራት ብልፅግና በሚመሠርተው መንግሥት ውስጥ በአስፈፃሚው አካልም ሆነ በፍርድ ቤቶች፣ በሌሎችም የፌደራልና የክልል ተቋማት ላይ ንቁ ተሣትፎ እንዲኖራቸው፤ በዘንድሮው ምርጫ በኃላፊነትና በብቃት የተወዳደሩ የሕዝብ አለኝቶችን ከዚህ በፊት ካደረግነው በእጅጉ ከፍ ባለና አዎንታዊ ለውጥ በሚፈጥር መልኩ እንደምናካትታቸው ለመግለጽ እወዳለሁ” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
“በዓባይ ጉዳይ በገፉን ቁጥር እየቆምን፣ በተጫኑን ቁጥር እየበረታን፣ ባዋከቡን ቁጥር ይበልጥ እየፀናን አሁን የደረስንበት ቦታ ላይ ቆመናል። በቅርቡ ሁለተኛውን ዙር የውኃ ሙሌት አድርገን በምርጫው ስኬት የተደሰትነውን ያህል በሕዳሴያችንም ሐሴት እንደምናደርግ አልጠራጠርም” ብለዋል።
“የትግራይ ሕዝብ በሚፈልገው መንገድ ከተደራራቢ ችግር የሚወጣበትን ተያያዥ ሀገራዊ ችግሮች የሚፈቱበትን እና ሰላምና ደኅንነት የሚረጋገጥበትን” ያሉትን የመፍትሔ አቅጣጫ እንደሚከተሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ በታሪክ ለውጥ ላይ መሆኗን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ “በዚህ ምርጫ የፈጠርነው አሸናፊና ተሸናፊን ሳይሆን ጠያቂና ተጠያቂ ያለበት የዲሞክራሲ ሥርዓትን ነው። በዚህ ደግሞ ያሸነፉት በምርጫው የተሳተፉት ሁሉም አካላት ናቸው። .... በዚህ ምርጫ ኢትዮጵያችን አሸናፊ ሆናለች” ብለዋል።
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5