ኤችአር 128 ተብሎ የሚጠራውን የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ላይ ያሳለፈውን ውሣኔ አስመልክቶ ያነጋገርናቸው የሕግ ባለሙያ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም ውሣኔው እንዳይፀድቅ ለማስተጓጎል የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰባት መቶ ሚሊየን ብር በላይ በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ማውጣቱን ገልፀውልናል።
በካሊፎርኒያ ስቴትስ ዩኒቨርሲቲ ሳንበርናርዲኖ የሕግ ፕሮፌሰሩ ዓለማየሁ ገብረማርያም ከአሜሪካ ድምፅ ጋር ባያደረጉት ቃለምልልስ ኤችአር128 የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት እርምጃዎችን ወደ መውሰድ እንዲያመራ የሚያደርገው ከሆነ በግለሰቦች ላይ ሊያነጣጥር እንደሚችልና በመብቶች ረገጣዎች ላይ እጃቸው አለ የሚባሉ ሰዎች ከታወቁ የአሜሪካ መንግሥት አሁንም ቢሆን ተግባራዊ በሆነው ማግኒትስኪ ሕግ መሠረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ኤችአር128 ኢትዮጵያ ውስጥ እየታዩ ናቸው የሚባሉ ለውጦችን ያደናቅፋሉ ብለው እንደማያስቡና እንዲያውም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከያዟቸውና እያንፀባረቋቸው ካሉ አቋሞች ጋር የሚደጋገፉ ናቸው የሚል እምነት እንዳላቸው ፕሮፌሰር ዓለማየሁ አመልክተዋል።
‘ኢትዮጵያ ለዩናይትድ ስቴትስ ቁልፍ አጋርና የአካባቢዋም የምጣኔ ኃብት ዕድገት፣ የሰላምና የፀጥታ መሪ መሆኗን ብንገነዘብም አልለቃት ያለው የሰብዓዊ መብቶች ረገጣዎቿ፤ በሲቪሎች ላይ በመንግሥቷ የሚካሄድ ሁከቷ፤ የጋዜጠኛነት ነፃነቶችን ማፈኗ፤ በዴሞክራሲያዊ መርኆች ጋር ፊትለፊት በሚጣረስ መንገድ ላይ መቆሟ፤ ሕገመንግሥቷን መጣሷ ያንን ሁሉ ከንቱ ያደርገዋል’ - ይላል የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት ሰሞኑን ያፀደቀው የውሣኔ ሰነድ 128።
ከፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም ጋር የተደረገውን ሙሉ ቃለ ምልልስ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5