ፍራንሲስ የኮንጎ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ደቡብ ሱዳን ሄዱ

  • ቪኦኤ ዜና

የሮማው ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፍራንሲስ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያደረጉትን የአራት ቀናት ጉብኝት አጠናቀው ዛሬ ዓርብ ለአስርት ዓመታት በዘለቀው ግጭት ወደ ታመሰችው ሌላዪቱ አገር፣ ደቡብ ሱዳን ሄደዋል።

የሮማው ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፍራንሲስ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያደረጉትን የአራት ቀናት ጉብኝት አጠናቀው ዛሬ ዓርብ ለአስርት ዓመታት በዘለቀው ግጭት ወደ ታመሰችው ሌላዪቱ አገር፣ ደቡብ ሱዳን ሄደዋል።

ሊቀ ጳጳሱ ደቡብ ሱዳንን በሚጎበኙበት ዋዜማ አገሪቱ ውስጥ በከብት አርቢዎችና በአካባቢዎች ሚሊሻዎች መካከል በተነሳ የበቀል ግጭት 27 ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል።

ከአጎራባቿ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ወደ ደቡብ ሱዳን ያቀኑት አቡነ ፍራንሲስ፣ ለአስርት ዓመታት የዘለቀው፣ በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የፈጀው እና በአብዛኛው በዘር ላይ የተመሰረው ግጭት እንዲያበቃ የሚያስችለውን የሰላም ሂደት ለማስጀመር ተስፋ አድርገዋል።

የ86ቱ ዓመት ሊቀ ጳጳስ እኤአ በ2013 ከጀመረው የጵጵስናው ዘመናቸው አንስቶ ከሰሃራ በታች ያሉትን የአፍሪካ አገር ሲጎበኙ ለሦስተኛ ጊዜያቸው መሆኑ ተመልክቷል።

በኮንጎው ቆይታቸው ቁጥራቸው እጅግ በበዙ ሰዎች አቀባባል የጠበቃቸው ቢሆንም የጦርነት፣ የድህነትና የረሀብ እውነታም ገጥሟቸዋል።

ሊቀ ጳጳሱ በደቡብ ሱዳኑ ጉብኝታቸው፣ ከዓለም አቀፉ የካንተርበሪ አንጀሊካን መሪ ጀስቲን ዌልቢ እና ከስኮትላንዱ ቤተክርስቲያን ጠቅላላ ጉባኤ አስተባባሪ ኢያን ግሪንሺልድስ ጋር ይቀላቀላሉ ተብሎ ተጠብቋል።

ሦስቱ የክርስቲያን መሪዎች “የሰላም ጉዞ” ብለው የጠሩትን ጉብኝት አንድ ላይ ሲያደርጉ በዓይነቱ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

ዌልቢ በጉብኝታቸው ዋዜማ የተፈጸመውን ግድያ “እጅግ አሰቃቂ” ነበር ብለውታል፡፡ ባስተላለፉት የትዊት መልዕክትም፣ ”በመላው ደቡብ ሱዳን ተዘውትሮ የሚሰማ ታሪክ ነው። አሁን በተለየ መንገድ እጠይቃለሁ ደቡብ ሱዳን ለሰላም ሲሉ አብረው እንዲሆኑ” ብለዋል።