አቡነ ፍራንሲስ በአፍሪካ ለአምስት ቀናት በሚያደርጉት ጉብኝታቸው ከኬንያ ሌላ ዩጋንዳና ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክም ይሄዳሉ፡፡
አቡኑ ናይሮቢው ጆሞ ኬንያታ ዓለምአቀፍ አይሮፕላን ጣቢያ ሲደርሱ የተቀበሏቸው የመንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ምዕመናን ናቸው፡፡
በኬንያ ቤተመንግሥት በተዘጋጀ ሥነ-ሥርዓት ላይ አቡነ ፍራንሲስ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታንና ዲፕሎማቶችን አግኝተዋል፡፡
ነገ፤ ሐሙስ አቡኑ ናይሮቢ በሚገኘው የቫቲካን ዲፕሎማሲያዊ ሚሲዮን ውስጥ የብዙ ኃይማኖቶች አባቶች እና ምዕመናን የሚገኙበትን የፀሎት ሥነ-ሥርዓት የሚመሩ ሲሆን በናይሮቢ ዩኒቨርሲቲም ተገኝተው እንዲሁ ፀሎትና አምልኮ ያደርጋሉ፡፡
አባ ፍራንሲዝ ናይሮቢ ውስጥ ከከተማዪቱ ጎስቋላ መንደሮች አንዱ የሆነውን ካንጌሚን የሚጎበኙ ሲሆን በካሣራኒ ስታዲየም ከወጣቶች ጋር ይገናኛሉ፡፡
አቡነ ፍራንሲዝ በሦስቱም ሃገሮች ውስጥ በሚያደርጉት ቆይታ በብርቱ ያሰጉኛል ያላቸውን የሰብዓዊ ጉዳዮችን አያያዝ ሁኔታ እንዲያነሱና እንዲመክሩ የጠየቀው ሂዩማን ራይትስ ዋች በደሎችንና ጥሰቶችን፣ እንዲሁም የስጋቱን አካባቢዎች ዝርዝር የያዘ ደብዳቤ ልኮላቸዋል፡፡
አቡኑ ፅንስ ላቋረጡ ሴቶች ያወጁትን ምኅረትና በረከት አሁንም እንዲያፀኑ፣ ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ ያለ ሴቶችን አግኝተው እንዲያናግሩና ከማኅበረሰብ ጤና ባለሙያዎች ጋርም ስለተዋልዶ ጤና እንዲመካከሩ ቡድኑ ጠይቋል፡፡
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡
Your browser doesn’t support HTML5
የፎቶ መድብላችንንም ይመልከቱ።