ዋሺንግተን ዲሲ —
ኮቪድ-19 በዓለም ዙሪያ በፈጠረው የጉዞዎችና የማመላለሻ መስተጓጎል ምክንያት በየሃገሩ መውጫ አጥተው የነበሩ አሜሪካዊያንን ከያሉበት በማውጣት የኢትዮጵያ አየር መንገድ እየሰጠ ላለው ያልተቋረጠ ድጋፍ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ስልክ ደውለው አመስግነዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያን ለመደገፍ ባላት ቁርጠኛነት እንደምትገፋና ለዓለምአቀፉ የጤና አጣዳፊ አደጋም ምላሽ ለመስጠት በዓለም ዙሪያ ካሉ አጋሮቿ ጋር መሥራቷን እንደምትቀጥል ሚኒስትር ፖምፔዮ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያረጋገጡላቸው መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ቢሮ ትናንት የወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በተጨማሪም በኢትዮጵያና በአሜሪካ ግንኙነቶች አስፈላጊነትና እንዲሁም ሁለቱ ሃገሮች የማይቋረጥ መተጋገዝ ሊያደርጉባቸው በሚገባ ቁልፍ በሆኑ አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይም መመካከራቸውን የቃል አቀባዩ መግለጫ አክሎ ጠቁሟል።