ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደቡብ ውለው እዚያው አደሩ

  • መለስካቸው አምሃ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በሀዋሳ

የመልካም አሰተዳደር ችግር ከአድራጎቶቻቸው ሊጠበቁ የሚገባቸው የፖለቲካ ነጋዴዎች የሚፈጥሩት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ዛሬ ተናግረዋል።

የመልካም አሰተዳደር ችግር ከአድራጎቶቻቸው ሊጠበቁ የሚገባቸው የፖለቲካ ነጋዴዎች የሚፈጥሩት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ዛሬ ተናግረዋል።

ለአሥራ አምስት ሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት በሆኑ የደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሦስት ከተሞች ውስጥ ሰሞኑን የተፈጠሩ ግጭቶችን አስመልክቶ ከከተሞቹ ነዋሪዎች ጋር ለመወያየትና የጋራ መፍትኄ ለማፈላለግ እዚያው የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ዛሬ ከሃዋሣና ከወላይታ ሶዶ ነዋሪዎች ጋር ውለዋል።

“የሲዳማ ሕዝብ ጠላቶች” ብለው የጠሯቸውን በፊቼ ጨምበላላ በዓል ወቅት ደም የፈሰሰበት ግጭት እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑ ሰዎችን ከሕዝቡ ጋር ሆነው ለፍርድ ለማቅረብ እንደሚሠሩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

እሥረኞችን በመልቀቅ በኩልም በፌደራል ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን አንስተው የደቡብ ሕዝቦች ክልልም በዚህ በኩል ሊንቀሳቀስ እንደሚገባው አሳስበዋል።

ሲዳማ በክልል ደረጃ እንዲዋቀር ሃዋሣ ላይ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ ሕዝቡ ጥያቄውን እንዲያነሣ ሕገመንግሥቱ እንደሚፈቅድ አመልክተው ክልል መሆን ለምን እንዳስፈለገ በሚገባ እንዲወያዩ መክረዋል።

በፌደራል ደረጃም በጥያቄው ላይ እንደሚወያዩ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሕገመንግሥታዊ አግባብ እንዲቀርብና ሕገመንግሥታዊ መፍትኄም እንደሚፈለግለት ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወላይታ ሶዶ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠሪዎች ጋር ያደረጉትን ውይይትም ዛሬ ያጠናቀቁ ሲሆን ነገ ወደ ወልቂጤ ሄደው በተመሣሣይ ሁኔታ እንደሚነጋገሩ የመንግሥትና ከገዥው ፓርቲ ጋር ቁርኝት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

Your browser doesn’t support HTML5

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደቡብ ውለው እዚያው አደሩ