የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት የአፍሪካ ኅብረትን የድርድር ጥሪ ተቀበሉ

የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት፤ አዲስ አበባ

የአፍሪካ ኅብረት በሳምንቱ መጨረሻ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት እና ህወሓት የሰላም ውይይት ለመጀመር ደቡብ አፍሪካ እንዲገኙ የጋበዘበትን የጥሪ ደብዳቤ ላከ።

የአሜሪካ ድምፅ የተመለከተው የአፍሪካ ኅብረት ደብዳቤ፣ ከመስከረም 28/2015 ዓ.ም አንስቶ በደቡብ አፍሪካ ሊካሄድ ለታቀደው የሠላም ንግግር፣ የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ግብዣ ማቅረባቸውን ያመለክታል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአፍሪካ ኅብረት የቀረበውን የድርድር ግብዣ የሚቀበሉ መሆናቸውን ትግራይን እያስተዳደረ ያለው ህወሓት መሪ ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል አስታውቀዋል።

በዶ/ር ደብረጺዮን ስም የወጣውና “የትግራይ መንግሥት የውጭ ጉዳዮች ቢሮ” የሚባለው አካል ማምሻውን ያሠራጨው መግለጫ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ማሃማት ፋኪ ባለፈው መስከረም 21 የላኩትንና ደቡብ አፍሪካ ውስጥ እንዲካሄድ ጥሪ ያደረጉበትን ግብዣ እንደሚቀበሉ አመልክቷል።

አክለውም “ይህ ግጭት በሰላም እንዲፈታ ቁርጠኞች ነን፤ ተደራዳሪ ቡድናችንን ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመላክ ዝግጁ ነን” ብለዋል።

ስለ ድርድሩ ግብዣ ቀድመው አለመማከራቸውን በደብዳቤያቸው ያመለከቱት የህወሓቱ መሪ ሌሎች የተጋበዙ አካላት ስለመኖር አለመኖራቸው፣ ታዛቢዎችና ዋስትና ሰጭዎች ስለመጋበዝ አለመጋበዛቸው፣ እንዲሁም የኅብረቱ ሊቀመንበር የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሚና ምን ሊሆን ይችላል ብለው እንደሚያስቡ፣ የተደራዳሪ ቡድናቸውን የጉዞና የደኅንነት ጥበቃ የመሳሰሉ የሎጂስቲክስ ሁኔታዎችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ማብራሪያዎችን እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል።

ድርድሩ የፊታችን ቅዳሜ መስከረም 28/2015 ዓ.ም ደቡብ አፍሪካ ውስጥ እንዲደረግ በግብዣው ላይ ከመጠቀሱ በስተቀር ትክክለኛው ቦታና ሰዓቱ እስካሁን ከየትኛውም ወገን አልተነገረም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ “የኢትዮጵያ አየር ኃይል ትናንት በአዲ-ዳዕሮ በሚገኙ ተፈናቃዮች ላይ ፈጽሟል” ባለው የድሮን ጥቃት፣ “65 ሰዎች ተገድለዋል፣ ከ70 በላይ የሚሆኑ ደግሞ ቆስለዋል” ሲል ህወሓት ዛሬ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡

ለዚህ ክስ፣ ከኢትዮጵያም ይሁን ከኤርትራ መንግሥት በኩል እስካሁን የተሰጠ ምላሽም ይሁን መግለጫ የለም፡፡

[ሙሉውን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ያገኛሉ]

Your browser doesn’t support HTML5

የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት የአፍሪካ ኅብረትን የድርድር ጥሪ ተቀበሉ