ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን እንዲለቁ መጠየቃቸው እና ሌሎችም የምክር ቤት ውሎዎች

Your browser doesn’t support HTML5

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን እንዲለቁ መጠየቃቸው እና ሌሎችም የምክር ቤት ውሎዎች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ሥልጣን እንዲለቁና የተወካዮች ምክር ቤትም እንዲበተን፣ ከአንድ የምክር ቤት አባል የተነሣውን ጥያቄ አጣጣሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ዛሬ፣ ሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በተካሔደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ፣ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በዛሬው መደበኛ ጉባኤ ላይ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተነሡላቸው ጥያቄዎች መካከል፣ የሚበዙት በሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡

በፌዴራል መንግሥት የተጀመረው የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ የማደራጀት ርምጃ፣ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ከዚኽም ጋራ ተያይዞ በዐማራ ክልል የተፈጠሩ ችግሮችን፣ በምን መልኩ ለመፍታት እንደታሰበም ጥያቄ ተነሥቷል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር የተፈጸመውን፣ የመኖሪያ ቤቶች እና የእምነት ተቋማት ፈረሳ በተመለከተ፣ ጥያቄ የተነሣላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ጉዳዩ በዋናነት፣ የከተማ አስተዳደሩ እና የኦሮሚያ ክልል ጉዳይ እንደኾነ ተናግረው፣ በሒደቱ የተጎዱ ሕጋዊ አካላት ካሉ ግን መካስ አለባቸው፤ ብለዋል፡፡

በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት ጉባኤ ላይ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ካነሡ አባላት መካከል የኾኑት ከዐማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ፓርቲ የተመረጡት ዶር. ደሳለኝ ጫኔ፣ ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ሁለንተናዊ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች፤ ያሉ ሲኾን፣ ለዚኽም የብልጽግናን መንግሥት ተጠያቂ አድርገዋል፡፡

በመኾኑም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን እንዲለቁ፣ ምክር ቤቱም እንዲበተንና ዐዲስ ምርጫ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከሥልጣን ይውረዱ” የሚል ጥያቄ፣ ከምክር ቤት አባል ሲቀርብላቸው፣ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡

በግጭቶች ምክንያት፣ ከተለያዩ ቦታዎች በማንነታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀዬአቸው ከመመለስ አንጻር ለተነሣላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ክልሎች ለዚኽ ተግባር፣ በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በዐማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል ያለው የመሬት ይገባኛል ውዝግብ ደግሞ፣ በሕዝበ ውሳኔ መፈታት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ከህወሓት ጋራ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ለማጽናት፣ መንግሥት የሚጠበቁበትን ሓላፊነቶች በመወጣት ላይ እንደኾነ ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋራ ተጀምሮ የተቋረጠው ድርድር በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለተነሣላቸው ጥያቄ ግን ምላሽ አልሰጡም፡፡ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ያላቸውን ወቅታዊ ግንኙነት በተመለከተም ጥያቄ ቢቀርብላቸውም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉት ነገር የለም፡፡

መንግሥት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ችላ በማለት፣ በፓርኮች ላይ የሚያደርገውን ኢንቨስትመንት በመተቸትም ጥያቄ የተነሣ ሲኾን፣ ለፓርኮች ግንባታ የሚውለው ገንዘብ፣ በተለያዩ ሀገራት እና ግለሰቦች ድጋፍ የተሸፈነ እንደኾነ ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢንቨስትመንቱ ለቱሪዝም ዘርፍ እድገት አስፈላጊ እንደኾነም አመልክተዋል፡፡

የሕዳሴ ግድብ ቀጣይ የውኃ ሙሌት፣ ከመስከረም ወር ወዲህ እንደማይከናወንና ይህም፣ የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡

ምክር ቤቱ፣ በዛሬ ስብሰባው፣ ለ2016 ዓ.ም. የቀረበለትን የ801 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር በጀትም አጽድቋል፡፡

አድማጮች፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የተነሡትን ጥያቄዎች እና የተሰጡትን ምላሾች፣ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።