የፍልስጤም ራስ ገዝ ፕሬዚደንት አዲሱን ካቢኔ አጸደቁ

የፍልስጤማውያን ራስ ገዝ ፕሬዚደንት ማህሙድ አባስ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር መመሀድ ሙስጠፋ

የፍልስጤማውያን ራስ ገዝ ፕሬዚደንት ማህሙድ አባስ በጠቅላይ ሚኒስትር መመሀድ ሙስጠፋ የቀረበውን አዲስ ካቢኔ ዛሬ ሐሙስ አጽድቀዋል፡፡

አዲሱ ካቢኔ ከጋዛ ጦርነት በኋላ የሚጫወተው ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ ካቢኔ ሥራውን እሁድ እንደሚጀምር የተናገሩ ሲሆን የጋዛ ጦርነት እንዲያበቃበትን ሁኔታ ቅድሚያ ይሰጠዋል ብለዋል፡፡

አክለውም ካቢኔያቸው "ለጋዛ ሃላፊነት መረከብን ጨምሮ ተቋማቱን እንደገና የማዋሃድ ራዕይን ለመቅረጽ ይሰራል" ሲሉ ተናግረዋል።

የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት ሶስት ወራት ባስቆጠረበት ባላፈው ጥር ወር ራማላህን የጎበኙት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ ፍልስጤማውያንን ተጠቃሚ ለማድረግ እና ዌስት ባንክን እና ጋዛን በአንድ ባለስልጣን ሥር እንዲተዳደሩ ለማስቻል “አስተዳደሩን መልሶ ማዋቀር” አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል፡፡

አዲሱ መንግስት 23 ሚኒስትሮችን ያቀፈ ሲሆን ከነዚህም መካከል ሶስት ሴቶች እና 6 ፍልስጤማውያን ከጋዛ የመጡ ናቸው፡፡

ከነዚህም መካከል የቀድሞ የጋዛ ከተማ ከንቲባ ማጌድ አቡ ረመዳን ይገኙበታል።

እ.አ.አ በ2007 ሐማስ በጋዛ ሥልጣኑን ከአባስ አስተዳደር ከነጠቀ ወዲህ በጋዛ ያለው ውጊያና ውድመት በፍልስጤም አስተዳደር ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ህዝብ ፊት የቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ ግልጽነት እንደሚያሰፍኑና ሙስናን እንደማይታገሱ ተናግረዋል፡፡

የፍልስጤም ራስ ገዝ በሙስና ቅሌቶች፣ በውስጥ ባለው መከፋፈል፣ በአምባገነናዊ ባህሪያቱ እና በእስራኤል ፍልስጤም የሰላም ስምምነትነት አለመሳካት የተነሳ ለረጅም ጊዜ መልካም ስም እንዳልነበረው ተመልክቷል፡፡

ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ከፍልስጤማውያን ጋር ለመስራት በጉጉት የሚጠባበቁ ዲሎማቶችን እምነት በማግኘት ረገድ አባስ በቅርቡ የወሰዷቸው ርምጃዎች እጅግ አነስተኛ መሆናቸውን የፈንረሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡