በዌስት ባንክ የነዳጅ ማደያ ላይ ጥቃት ቢያንስ አራት ሰዎች ተገደሉ

  • ቪኦኤ ዜና
የእስራኤል ፖሊሶች

የእስራኤል ፖሊሶች

እስራኤላውያን ሰፋሪዎች ከሚገኙበት መንደር አቅራቢያ ካለ የነዳጅ ማደያ ላይ፣ አንድ ታጣቂ በከፈተው ተኩስ፣ ቢያንስ አራት ሰዎች መገደላቸውንና በጽኑ የቆሰሉትን ሁለቱን ጨምሮ በጠቅላላው ሌሎች ስድስት ሰዎች የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው፣ የእስራኤል የሕክምና ባለሞያዎች ገለጹ።

ጉዳት ያደረሰውን ታጣቂ መግደላቸውን ይፋ ያደረጉት፣ የእስራኤል የጸጥታ ኃይሎች፣ በዛሬው ዕለት እንዳስታወቁት፣ ከፍልስጥኤሟ የራማላ ከተማ በስተሰሜን ከሚገኘው፣ ኢላይ የተባለ የአይሁዶች ሠፈር አቅራቢያ፣ ጥቃት ያደረሱ ሌሎች ታጣቂዎችን ለመያዝ አሰሳ ይዘዋል።

የማክሰኞው ጥቃት፥ የእስራኤል ጦር ሠራዊት፣ ትላንት በሰሜናዊ ዌስት ባንክ የጀመረውና ስድስት ፍልስጥኤማውያን ተገድለው፣ በደርዘን የሚቆጠሩ የቆሰሉበትን ወታደራዊ አሰሳ ተከትሎ የተቀሰቀሰ ነው። ግጭቱ፣ ለዓመታት ከታዩት ሁሉ የበረታ እንደኾነ ተነግሮለታል።

በተያያዘ ዜና፣ የእስራኤል ጦር ሠራዊት፣ በተለይ በዌስት ባንኳ የጄኒን ከተማ፣ ባልተለመደ መልኩ ወታደራዊ ሄሊኮፕተሮችን እንዳሠማራ ተዘግቧል።