ቅዱስ ሲኖዶስ በትግራይ ክልል ይፈጸማል የተባለውን የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እንዲያስቆም መንግሥትን ጠየቀ

Your browser doesn’t support HTML5

ቅዱስ ሲኖዶስ በትግራይ ክልል ይፈጸማል የተባለውን የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እንዲያስቆም መንግሥትን ጠየቀ

ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ትላንት ተሲዓት በኋላ የጀመረውን አስቸኳይ ስብሰባ፣ ዛሬ ቀትር ላይ ሲያጠናቅቅ ባወጣው ባለአራት ነጥብ መግለጫ፣ በትግራይ በሚገኙ አራት አህጉረ ስብከት የተመደቡ አባቶች፣ ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ሊፈጽሙ ያቀዱት የኤጲስ ቆጶስ ሢመት፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ያልተከተለ በመኾኑ መንግሥት እንዲያስቆመው ጥሪ አቀረበ፡፡ ችግሩ የሚፈታበትን የውይይት መድረክ በማመቻቸትም እንዲያግዝም ጠይቋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ትላንት እና ዛሬ አስቸኳይ ጉባኤ ማድረጉን ያመለከተው መግለጫው፣ በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመታት በተካሔደው ጦርነት ምክንያት፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ መዋቅር እና በትግራይ አህጉረ ስብከት መካከል የነበረው አስተዳደራዊ ግንኙነት ተቋርጦ መቆየቱን ይጠቅሳል፡፡ ይህን ተከትሎ የተፈጠረው አለመግባባት በውይይት እንዲፈታ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሀገራዊ የሰላም እርቁ ከተፈጸመበት ማግሥት ጀምሮ በተደጋጋሚ በደብዳቤ ሲጠየቅ መቆየቱን ያወሳል፡፡

ኾኖም፣ ጥረቱ ሳይሳካ ቀርቶ፣ በክልሉ ያሉት ሊቃነ ጳጳሳት፣ መዋቅራዊ አደረጃጀቱን በመጣስ፣ “መንበረ ሰላማ የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት” መሥርተናል ማለታቸውን መግለጫው አውስቷል፡፡ የፊታችን ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. 10 ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም ቀጠሮ እንደያዙ፣ ለብዙኃን መገናኛ መግለጫ መስጠታቸውን ይናገራል፡፡

በመግለጫው ላይ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ማብራሪያ የሰጡት የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አባ ጴጥሮስ፣ ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅመው አንድነት ስለኾነ፣ በሰላም እና በፍቅር ለአንድነት እንሥራ፤ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ሙሉ ዘገባን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።