በኦሮሚያ ክልል፣ በግጭት ውስጥ ባሉት የመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች የተኩስ ልውውጥ እና ውንጀላዎች፣ ለእንግልት እና ጉዳት እየተዳረጉ እንደኾነ፣ የአሜሪካ ድምፅ በስልክ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገለጹ።
“መንግሥትን ትደግፋላችኹ” በሚለው የታጣቂዎች ውንጀላ እና “ታጣቂዎቹን ትደግፋላችኹ” በሚለው የመንግሥት ክስ መካከል እየተንገላቱ እንደኾነ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
በክልሉ ምዕራብ ወለጋ ዞን በቆንዳላ እና ቤጊ ወረዳዎች፣ ባለፈው ሳምንት ኀሙስ እና ትላንት እሑድ፣ ሁለት ሰዎች እንደተገደሉ የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ ለግድያው የመንግሥት የጸጥታ ኀይሎችን ተጠያቂ አድርገዋል።
በሌላ በኩል፣ ከዐዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ ከምትገኘው ሙከጡሪ ከተማ፣ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች 15 ሰዎችን አግተው እንደወሰዱ ነዋሪዎቹ አመልክተዋል።
የክልሉ መንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ቢሮ፣ ለዚኽ ክስ በቀጥታ የሰጠው ምላሽ ባይኖርም፤ ከቀናት በፊት የቢሮው ሓላፊ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት አስተያየት፣ ለሰላማውያን ዜጎች ግድያ እና እገታ ታጣቂ ቡድኑን ተጠያቂ አድርገዋል። ታጣቂ ቡድኑ ግን የሚቀርብበትን ክስ በተደጋጋሚ ያስተባብላል።
ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።