ከምሥራቃዊ የዐማራ ክልል ወደ ዐዲስ አበባ መግባት ያልቻሉ መንገደኞች ቅሬታ አሰሙ

Your browser doesn’t support HTML5

ከምሥራቃዊ የዐማራ ክልል ወደ ዐዲስ አበባ መግባት ያልቻሉ መንገደኞች ቅሬታ አሰሙ

“ከምሥራቃዊው የዐማራ ክልል ወደ ዐዲስ አበባ እንዳንገባ፣ በኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ኃሎች ተከለከልን፤” ሲሉ መንገደኞች ቅሬታ አቀረቡ፡፡

አስተያየት ሰጭዎች እንደጠቆሙት፣ ክልከላው፣ ዓመታዊው የኢሬቻ በዓል መቃረቡን ተከትሎ የተጀመረ ነው፡፡ በክልከላው ምክንያት፣ ለዐዲስ ሥራ የቃለ ምልልስ እና የሕክምና ቀጠሮዎች ያላቸው ተጓዦች እንደሚገኙበት ተመልክቷል፡፡

በዐማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን የሕዝብ ትራንስፖርት መናኸሪያ አስተዳደር፣ የፌዴራል መንገዶች በፌዴራል እንጂ በክልል የጸጥታ ኀይሎች መጠበቅ እንደሌለባቸው ገልጾ ድርጊቱን ተቃውሟል፡፡ አስተዳደሩ አያይዞም፣ እንዳያልፉ የተከለከሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ የዐማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከኦሮሚያ ክልል ጋራ ባደረገው የጸሑፍ ልውውጥ፣ ወደሚማሩበት አካባቢ ጉዟቸውን እንዲቀጥሉ መደረጉን ገልጿል፡፡

የዐማራ ክልል ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዋና ዲሬክተር፣ በጉዳዩ ላይ ከኦሮሚያ ክልል እና ከዐዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮዎች ጋራ እንደተወያየ ጠቅሶ፣ “ፍተሻ እንጅ ክልከላ አላደረግንም፤” የሚል ምላሽ እንደደረሳቸው፣ ዋና ዲሬክተሩ ዘውዱ ማለደ አስታውቀዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሓላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱም፣ “ጸጥታ ለማስከበር ተጓዦችን ፈተሽን እንጂ ክልከላ አላደረግንም፤” ብለዋል፡፡

ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።