የልዩ ኃይል አባላትን ወደ ልዩ ልዩ የጸጥታ ተቋማት በማስገባት መልሶ የማደራጀት ተግባር በማከናወን ላይ መኾኑን የገለጸው የኦሮሚያ ክልል፣ የልዩ ኃይል አደረጃጀትን ሥምሪት ማቆሙን፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ አስታወቁ።
የክልሉን የጸጥታ ማስከበር ሥራም፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ መረከባቸውን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ መልኩ፣ የደቡብ እና የሶማሌ ክልሎችም፣ በፌዴራል መንግሥት የተላለፈውን የልዩ ኃይል መዋቅራዊ ለውጥ ውሳኔ በመተግበር ሒደት ላይ መኾናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የልዩ ኃይል አባላቱ፣ በመደበኛ የጸጥታ ተቋማት ማለትም በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በፌዴራል ፖሊስ ሠራዊት እና በክልሎች ፖሊስ ሠራዊት ውስጥ እንደሚካተቱ የየክልሎቹ አመራሮች አስረድተዋል።
“የልዩ ኃይል አባላትን ወደ ልዩ ልዩ የጸጥታ ተቋማት በማስገባት መልሶ የማደራጀት ፕሮግራም” በሚል በፌደራል መንግሥት መንግሥት የተላለፈው ውሳኔ፣ በኦሮሚያ ክልል ወደ ትግበራ ምዕራፍ መግባቱን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽነሩ አራርሳ መርዳሳ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ሲናገሩ፣ የመንግሥትን የመዋቅራዊ ለውጥ ውሳኔ መነሻ ያደረገው የኦሮሚያ ክልል፣ የልዩ ኃይል አባላትን ቅጽ በማስሞላት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
“የልዩ ኃይል አባላት፣ በሀገር ደረጃ ወደ ጸጥታ ተቋማቱ ለመግባት በተቀመጠው መስፈርት መሠረት፣ እንደ ፍላጎታቸው ቅጽ እየሞሉ ይገኛሉ፤” ሲሉ አተገባበሩን አስረድተዋል፡፡
“በፈዴራል መንግሥት ውሳኔ ተወስኖ ወደ ሥራ እንድንገባ አቅጣጫ ከተቀመጠ ወዲህ ፤ ከአመራር እስከ ልዩ ኃይል አመራሮች እና ስምሪት ሰጭዎች በየደረጃው ውይይት ተካሂዶበታል። ውይይቱ በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን እና ከክልሉ ፀጥታ መዋቅር ጋራ በተቀናጀ መልኩ ተደርጓል። በውይይቱ መግባባት ላይ ከተደረሰ በኋላ የልዩ ኃይሉን መዋቅር መልሶ ለማደራጀት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እየተከናወነ ነው። በሂደቱ ያጋጠመን ችግር የለም።”
በዚኽም መሠረት ክልሉ፣ የልዩ ኃይልን ሥምሪት ማቆሙን ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ ተናግረዋል፡፡
“ይህ ኃይል በመረጠው የፀጥታ ኃይል መዋቅር ተቀላቅለው እንዲሠሩ ከተወሰነ ወዲህ ለውጥ እየተደረገ ስለኾነ እንደ ከዚህ ቀደሙ ተደራጅቶ የሚንቀሳቀስ ኃይል አይኖርም። እንደየ እዛቸው ወጥተው ወደ ተለያየ የፀጥታው ዘርፍ ለመቀላቀል ሂደት ላይ ናቸው። ስለዚህ አኹን በክልሉ የልዩ ኃይል ስምሪት የለም።”
“ልዩ ኃይሉ ወደ መረጠው እንዲቀላቀል ምዝገባ እየተካሄደ ነው። ነገር ግን መከላከያ ሠራዊትን መቀላቀል የሚፈልገው ስለ ፈለገ ብቻ ሳይሆን መስፈረቱን አሟልቶ ሲገኝ ነው የሚቀላቀለው። ወደ ሌሎች መዋቅሮችም የሚቀላቀሉት በዚሁ መሰረት ነው። አልፈለገም ያለም መብቱ ተከብሮለት መቋቋምያ ተሰጥቶ ይሰናበታል።”
የኢትዮጵያ መንግሥት “ሸኔ” በሚል በአሸባሪነት ከፈረጀው እና ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጋራ የሚያካሒደው ውጊያ፣ በኦሮሚያ ክልል ከሚታዩ የጸጥታ ችግሮች አንዱ ነው።
ከዚኹ የጸጥታ ችግር ጋራ በተያያዘ፣ “የፌዴራሉ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ልዩ ኃይልን በመተካት፣ በኹሉም አካባቢ ተሰማርተዋል፤” ብለዋል ።
“እንደ ኦሮምያ ክልል ሸኔ የተደረገለትን የሰላም ጥሪ ባለመቀበሉ የክልሉ ፀጥታ እንዳይ ታወክ የፀጥታው ኃይል በክልሉ ተሰማርቷል። በክልሉ ሁሉም አካባቢ የሀገር መከላከያ ፣የፈዴራል ፖሊስ ፣መደበኛ ፖሊስ እና የአካባቢው ሚሊሻ ተቀናጅተው ይሠራሉ”
በሌላ በኩል ፣ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልልም፣ የልዩ ኃይል መዋቅሩን በውሳኔው መሠረት መልሶ የማደራጀት ሥራ መጀመሩን፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ዓለማየሁ ማሞ ተናግረዋል።
የሶማሌ ክልል ፕረዚዳንት ሙስጠፌ መሐመድ፣ በትዊተር ገጻቸውእንዳሰፈሩት፥ የክልሉ ካቢኔ፣ የልዩ ኃይል መዋቅርን መልሶ የማደራጀት ውሳኔ አስፈላጊነት ላይ ተወያይቶ ማጽደቁን ገልጸዋል።
የኹሉንም ፌዴራላዊ ክልሎች የልዩ ኃይል አባላትን፣ ወደ መደበኛ የጸጥታ ተቋማት የማስገባት ፕሮግራም፣ በመላ አገሪቱ እንደሚተገበር የኢትዮጵያ መንግሥት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ለፕሮግራሙ አተገባበርም በመንግሥት አቅጣጫ መቀመጡን፣ ለአሜሪካ ድምፅ የተናገሩት የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ፣ በልዩ ልዩ ደረጃ ከሚገኙ የጸጥታ አመራሮች ጋራ ውይይት እንደተደረገበትና ይህም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወን እንደኾነ አክለው ገልጸዋል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።