የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ማዕከላዊ ዞን በኦሮሚያ ክልል ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት “ዝግጁ” መሆኑን በመልካም እንደሚቀበሉ የክልሉ ፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ትላንት በፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ አስታውቀዋል።
ክልሉ ከቡድኑ ጋራ ሊደረግ ለሚችል የሰላም ንግግር “ሁሉንም አስፈላጊ ሁኔታዎች” ይፈጥራል ያሉት ፕሬዝደንቱ፣ ክልሉ ከየትኛው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የማዕከላዊ ዞን አዛዥ ጋራ እንደተገናኘ በስም አልጠቆሙም።
የአቶ ሽመልስ አብዲሳ መግለጫ የተሰማው ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አዛዦች ውስጥ አንዱ የሆኑት ጃል ሰኚ ነጋሳ በክልሉ ያለው ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ፍላጎት እንዳላቸው በገለጹ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ነው።
በኢትዮጵያ ወታደራዊ ባለሥልጣናት በተመቻቸና፣ ከተመረጡ የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች ጋራ ከሁለት ሳምንት በፊት በተደረገ የስልክ ውይይት ላይ፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የቀድሞው የማዕከላዊ ዞን አዛዥ የነበሩት ጃል ሰኚ ነጋሳ፣ ጃል መሮ ወይም ኩማ ድሪባ በሚል ከሚታወቁት የሠራዊቱ ዋና አዛዥ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አቋርጫለሁ ብለዋል።
የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፣ ጠቅላይ ምኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ ከስደት ወደ ሃገር ቤት ከተመለሰውና ታግዶ ከነበረው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የተገነጠለ ቡድን ነው። ቡድኑ ያሉት ቅሬታዎች “የኦሮሞ ሕዝብ መገለል ይደርስበታል” እንዲሁም “በፊዴራል መንግስትም ትኩረት አይሰጠውም” የሚል እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል።
በኦነግና በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት መካከል በታንዛንያዋ ከፊል ራስ ገዝ የዛንዚባር ደሴት ላይ ባለፈው ዓመት የተደረገው የሰላም ንግግር ካለ ውጤት ተበትኗል።