በኦሮሚያ የኮሌራ ወረርሽኝ እየተዛመተ ነው

Your browser doesn’t support HTML5

በኦሮሚያ የኮሌራ ወረርሽኝ እየተዛመተ ነው

· 3ነጥብ 3 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ወረርሽኙ ያሰጋቸዋል

· ኦቻ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት አስቸኳይ ድጋፍ ጠይቋል

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባባሪያ ቢሮ(ኦቻ)፣ በኦሮሚያ ክልል በአምስት ዞኖች የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ መከሠቱን አስታወቀ።ኦቻ ሰሞኑን በአወጣው መግለጫ፣ በክልሉ፥ ምሥራቅ ባሌ፣ ጉጂ እና ቦረና ዞኖች፣ 50 ሰዎች በወረርሽኙ መሞታቸውን ጠቅሷል፡፡

በኢትዮጵያ 3ነጥብ3 ሚልዮን ዜጎች፣ በኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ ስጋት ውስጥ መኾናቸን የጠቀሰው ኦቻ፣በመዛመት ላይ ለሚገኘው ወረርሽኝ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት አስቸኳይ ድጋፍ ጠይቋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ በበኩሉ፣ የኮሌራ በሽታ፣ በአምስት ዞኖች በወረርሽኝ ደረጃ መከሠቱን አረጋግጧል፡፡የጉጂ እና የምሥራቅ ባሌ ወረዳ ነዋሪዎች፣ በሽታው በፍጥነት በመስፋፋት ላይ እንዳለ ገልጸው፣ አፋጣኝ የሕክምና አገልግሎት እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባባሪያ ቢሮ(OCHA)፣ መጋቢት 23 ቀን 2023 በአወጣው ሪፖርቱ ነው፣ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አምስት ዞኖች የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ መከሠቱን ያስታወቀው፡፡
ኦቻ፣ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ባሌ፣ ጉጂ እና ቦረና ዞኖች የተስፋፋው የኮሌራ ወረርሽኝ፣ ሪፖርቱ እስከ አወጣበት ጊዜ ድረስ፣ በአጠቃላይ 2ሺሕ276 የኮሌራ ተጠቂዎች ሲመዘገቡ፣ የ50 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ጠቅሷል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሓላፊ እና የኅብረተሰብ ጤና ስጋት አመራር እና የላብራቶሪ ዘርፍ አስተባባሪ ዶ/ር ተስፋዬ ክበበው፣ ወረርሽኙ እየተስፋፋባቸው ያሉ ዞኖች፣ ቆላማ እና በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች ናቸው፤ ብለዋል፡፡

“በአምስት ዞኖች ውስጥ በሽታዉ ተከስቷል ።ባሌ፣መስራቅ ባሌ፣ጉጂ፣ቦረና እና ምዕራብ አርሲ ውስጥ ነዉ ወረርሽኙ የተከሰተው ።ከአምስቱ ዞኖች ሁለት ዞኖች ወረርሽኙን የመቆጣጠር ሁኔታ እየታየ ነዉ።ነገር ግን ሁለት ዞኖች ማለትም ቦረና ጉጂ ዉስጥ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።”

በምሥራቅ ባሌ ቆላማ ወረዳዎች ውስጥ፣ ሰሞኑን መዝነም የጀመረውን ዝናም ተከትሎ፣ በሽታው በፍጥነት እየተስፋፋ እንደሚገኝ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ አቶ አልይ አሕመድ ለአሜሪካ ድምፅ የገለጹትም ይህንኑ ነው፡፡

“ቆላማው አካባቢ ያሉት ወረዳዎች በሙሉ በኮሌራ የተበከሉ ናቸዉ።ደዌ ሰረር፣ዳዌ ጋቻን፣ ራይቱ ፣ጊንር እንድሁም ለጋ ህዳ አደሌ ሀረ የሚባል ቦታ አሁን የጠቀስኳቸው ቦታዎች ላይ በሽታው በስፋት ታይቷል።በመንግስት በኩል ህክምና እየተሰጠ ነዉ።ነገር ግን ከህዝብ ብዛት ጋር አይመጣጠንም ።በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ለይቶ ማቆያ ውስጥ እያደረጉ ነዉ፤ አሁንም ግን ህክምናዉ መጠናከር አለበት፣ ይቀራል ።”

ኦቻ በአወጣው ሪፖርት መሠረት፣ ከጥር 2023 መጨረሻ ጀምሮ፣ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች፣ የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ በእጥፍ ጨምሯል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በባሌ፣ ጉጂ እና ምዕራብ አርሲ ዞኖች በሚገኙ 66 ቀበሌዎች፤ በሶማሌ ክልል ደግሞ በሊበን ዞን ኹለት ወረዳዎች፣ በድምሩ 1ሺሕ055 የተጠቁ ሰዎች ሪፖርት ተደርጓል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የኮሌራ በሽታ፣ በ22 ወረዳዎች በሚገኙ 177 ቀበሌዎች መሠራጨቱንና ከእነዚኽ ውስጥ 18ቱ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ እንደኾኑ፣ ኦቻ ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት አገኘኹት ያለውን መረጃ ጠቅሷል፡፡

የኦሮምያ ጤና ቢሮ በበኩሉ፣ ከነሐሴ 27 ቀን 2022 ጀምሮ፣ በባሌ ቆላማ አካባቢ፣ ሀረና ቡልቅ ወረዳ የተከሠተው ወረርሽኙ፣ እየተስፋፋ በአሁኑ ወቅት በአምስት ዞኖች ውስጥ መዳረሱ ገልጿል።በበሽታው የ50 ሰዎች ሕይወት ማለፉንና ከ2ሺሕ በላይ ሰዎች በበሽታው ለሕመም መዳረጋቸው ተገልጿል፡፡ ሥርጭቱ እንዳይስፋፋ፣ የክልሉ ጤና ቢሮ እየሰራ ነው፤ ብለዋል የዘርፍ አስተባባሪው ዶ/ር ተስፋዬ።
“ጊርጃ ወረዳ፣ወደራ፣አዶላ ሬዴ ውስጥ በሽታው ተከስቷል ።አሁን ወደራ ወረዳ ውስጥ ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች በበሽታዉ ተጠቅተዋል።እናም ከፍተኛ ችግር እያስከተለ ነዉ ።የበረታባቸዉ ሰዎችም ህይወታቸው እያጡ ነዉ ።በተለይ ወደራ ወረዳ አሁንም ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ነዉ ያለዉ ።እየተሰጠ ያለዉ ህክምና በጥቂት አይደለም ።በዘመቻ መልክ ህብረተሰቡ ዘንድ መደረሰ ግዴታ ነዉ።
የጉጂ ዞን ነዋሪ መኾናቸውን የጠቀሱት ስማቸው እንዳይገለጽ ያሳሰቡን ግለሰብ፣ በዞኑ ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን ተናግረዋል።”

“በበሽታው የተያዘ ሰዉ ካለ መለየት ነዉ፣ከተለዩ በሗላ ሰውዬው ጋር መድረስ እና እዛ አካበቢ ያለዉን ሁነታ ሪፖርት ማድረግ ነዉ።ከዛም አካባቢው ላይ ያለዉን ንክኪ መለየት እና አስፈላጊውን የህክምና መስጠት ይጀመራል።ነገር ግን በበሽታዉ የተጠቃ ሰዉ ሲገኝ ለይቶ የማስቀመጥ ስራ ይከናወናል።አሁንም በሽታዉን ለመግታት አስፈላጊው ስራ እየተሰራ ነዉ።”

ኮሌራ ተላላፊ መኾኑን ያስገነዘቡት ዶክተር ተስፋዬ፣ ኅብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ከገዳዩ በሽታ ራሱንና ቤተሰቡን እንዲከላከል ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ 3ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች፣ በኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ ስጋት ውስጥ እንደኾኑ የጠቀሰው ኦቻ፣ ለተከሠተው ወረርሽኝ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ይችል ዘንድ አስቸኳይ ድጋፍ ጠይቋል፡፡