ለወራት የታሰሩ ሦስት የብዙኀን መገናኛ ባለሞያዎች ተፈቱ

አዲስ አበባ

አካልን ነጻ የማውጣት ክስ የመሠረቱ ሦስት የብዙኀን መገናኛ ባለሞያዎች መለቀቃቸውን ጠበቃቸው አስታወቁ፡፡

ሦስቱ የብዙኀን መገናኛ ባለሞያዎች፣ በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ዐውድ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውለው በወራት ለሚቆጠር የተለያየ የጊዜ መጠን፣ በአዋሽ አርባ እና በአዲስ አበባ ታስረው መቆየታቸውን፣ ከጠበቆቻቸው አንዱ ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ዐዲሱ ጌታነህ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል፡፡

ከሦስቱ መካከል፣ በቃል አላምረው እና በላይ ማናዬ፣ ዛሬ ሰኞ፣ ሲፈቱ ቴዎድሮስ ዘርፉ ደግሞ ከትላንስት በስቲያ ቅዳሜ መፈታቱን ጠበቃቸው አቶ ዐዲሱ ጌታነህ ገልጸዋል፡፡

SEE ALSO: መንግሥት የብዙኀን መገናኛ ዐዋጁን እንዲያከብር ባለሞያዎች ጠየቁ

ሦስቱን የብዙኀን መገናኛ ባለሞያዎች ጨምሮ አራት እስረኞች፣ በጠበቆቻቸው አማካይነት፣ ባለፈው ማክሰኞ ሰኔ 4 ቀን፣ አካልን ነጻ የማውጣት ክስ መሥርተው ነበር፡፡

ፖሊስ፣ እስረኞቹን ነገ ማክሰኞ፣ ሰኔ 11 ቀን እንዲያቀርባቸው፣ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡

ባለፈው ዓመት፣ ሐምሌ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር የዋለው በቃል አላምረው፣ ከ10 ወራት በላይ የታሰረ ሲኾን፣ ቴዎድሮስ ዘርፉ ለ10 ወራት ያህል፣ በላይ ማናዬ ደግሞ ከሰባት ወራት በላይ፣ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቆይተው ነው የተለቀቁት፡፡

በሌላ በኩል፣ “ሁከት እና ብጥብጥ በማሥነሳት ወንጀል ጠርጥሬአቸዋለኹ” በሚል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያደረገባቸው የሚገኙት፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ(ኢሕአፓ) ሊቀ መንበር ዝናቡ አበራን ጨምሮ ዘጠኝ ታሳሪዎች፣ በገንዘብ ዋስ እንዲፈቱ፣ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት፣ ዛሬ ሰኞ፣ ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ወስኗል፡፡

Your browser doesn’t support HTML5

ለወራት የታሰሩ ሦስት የብዙኀን መገናኛ ባለሞያዎች ተፈቱ

የኀይል ጊዜው ባበቃው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዐውድ ሥር የተያዙት እስረኞቹ፣ ባለፈው ሳምንት የሥር ፍርድ ቤት ለፖሊስ የሰጠውን የ12 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመቃወም፣ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ያቀረቡት ይግባኝ ተቀባይነት አግኝቶ ነው የዋስትና መብት የተፈቀደላቸው፡፡

ታሳሪዎቹ ባቀረቡት ይግባኝ ላይ፣ ጠበቆቻቸው እና ፖሊስ፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ ክርክር ያደረጉ ሲኾን፣ ፖሊስ በቂ የምርመራ ጊዜ እንደነበረው በማመን፣ ከፍተኛው ፍርድ ቤት፣ የሥር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ መሻሩን፣ ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ሰሎሞን ገዛኸኝ አስረድተዋል፡፡

የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች፣ የዋስትናውን ገንዘብ አስይዘው የመፍቻ ትእዛዝ በመያዝ፣ ከቀትር በኋላ እስረኞቹ ወደሚገኙበት ፖሊስ ጣቢያ አምርተው ለሰዓታት መጠበቃቸውን የገለጹት፣ የኢሕአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበሩ መጋቤ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት፣ ኾኖም እስከ ቀኑ 11 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ድረስ ታሳሪዎቹ እንዳልተለቀቁ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ዋስትና ከተፈቀደላቸው ታሳሪዎች ውስጥ፣ ከመጋቢት 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙት የኢሕአፓ ሊቀ መንበር ዝናቡ አበራን ጨምሮ አምስቱ “የእርስ በእርስ ጦርነት ይብቃ” በሚል መሪ ቃል፣ ላለፈው ኅዳር 30

ቀን 2016 ዓ.ም. ተጠርቶ የነበረውን ሰላማዊ ሰልፍ ሲያስተባብሩ ከነበሩት ፖለቲከኞች መካከል መኾናቸውን፣ መጋቤ ቢሉይ አብርሃም ገልጸዋል፡፡

የሰልፉ አስተባባሪ መኾናቸውን በይፋ በፊርማቸው ካረጋገጡ 13 ፖለቲከኞች መካከል፣ ከዚኽ ቀደምም በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ዐውድ ሥር አምስቱ፣ በተለያዩ ጊዜያት ለተለያየ የጊዜ መጠን ታስረው መለቀቃቸውን መዘገባችን ይታወቃል፡፡