የመገንጠል ጥያቄን ከፕሮግራሙ እንዳስወጣና በኢትዮጵያ ለዴሞክራሲና ለእኩልነት እንደሚታገል የገለፀው ኦሮሞ ነጻነት ግንባር ቡድን መሪ ጄነራል ከማል ገልቹ አሁን የደረስንበት ውሣኔ አዲስ ሳይሆን ለአርባ ዓመታት ከድርጅቱ ጋር የኖረ ነው ብለዋል። በድርጅቱ ውስጥ ሃሣቦች መሸናነፍ ስላልቻሉ ረጅም ጊዜ ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር ጋር ከመጓዙም በላይ ሰፊ ያለመግባባት ምንጭም ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም “የኦሮሚያ ነፃ መንግሥት መመሥረት ወይንም የኦሮሞ አጎራባች ከሆኑ ህዝቦች ጋር በመከባበርና በመፈቃቀድ አንድ አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ገንብቶ አብሮ መኖር፤ ሁለቱንም ሃሣቦች ድርጅቱ በአንድ ገፅ ላይ እንደ ፖለቲካ ፕሮግራሙ የተቀበለ መሆኑን” እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2004 ዓ.ም አፅድቀናል ብለዋል።
ሆኖም በዚያን ወቅት “ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በአንድነት ለዴሞክራሲ እንታገል የሚለው የብዙ አባላት ድጋፍ የነበረው ሃሣብ ‘የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ሙሉ በሙሉ መረጋገጥ’ በሚል ሃሳብ ሥር ነው እንዲደበቅ የተደረገው” ብለዋል።
በመሠረቱ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር ውስጥ የነበረው ልዩነት “የኦሮሞ ህዝብን ጥያቄ በምን ዓይነት መልክ ብናስቀምጠው ነው የበለጠ ውጤታማ የምንሆነው?” የሚለው እንደሆነና ለረጅም ጊዜም መልስ ሳይገኝ እንደኖረ ተናግረዋል።
ጄነራል ከማል ገልቹ በ “ለጥያቄዎ መልስ” ዝግጅታቻን ላይ ቀርበው ለአድማጮች ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል፡፡ ያዳምጡት፡፡