ታዋቂው የቀድሞ የእግር ኳስ ተጫዋች፣ እንዲሁም የቀድሞ የትዳር አጋሩን ገድሏል በሚል ከ30 ዓመታት በፊት ከቀረበበትና “የክፍለ ዘመኑ የፍርድ ሂደት” በመባል ከሚታወቀው ክስ ነፃ የወጣው ኦ ጄ ሲምፕሰን፣ በ76 ዓመቱ ትላንት ረቡዕ ላስ ቬጋስ ውስጥ ከዚሕ ዓለም በሞት መለየቱን ጠበቃው አስታውቀዋል።
ሲምፕሰን የካንሰር ሕመምተኛ እንደነበርም ጠበቃው ቲ ኤም ዚ ለተባለው ቴሌቪዥን አስታውቀዋል።
በአሜሪካ የእግር ኳስ ጨዋታ ከፍተኛ ዝናን አትርፎ የነበረው ሲምፕሰን፣ በእ.አ.አ 1994 የቀድሞ የትዳር አጋሩን፣ ኒኮል ብራውን ሲምፕሰንን እና ጓደኛዋ የነበረን አንድ ሌላ ግለሰብ ገድሏል በሚል የቀረበበት ክስና የፍርድ ቤት ሂደት፣ የአሜሪካውያንንም ሆነ የተቀረውን ዓለም ትኩረት ሰቅዞ የያዘ ነበር።
ሲምፕሰን፣ ጥቁር፤ የቀድሞ ባለቤቱ ደግሞ ነጭ መሆኗ፣ አሜሪካዉያን የፍርድ ሂደቱን በውጥረት ውስጥ ሆነው እንዲከታተሉት አድርጓል።
ሲምፕሰን ከመጀመሪያው ክስ ቢያመልጥም፣ ውድ የስፖርት ማስታወሻዎችን የሚሸጡ ደላላዎችን በመሣሪያ አስፍራርቶ ዘርፏል በሚል ከአሥር ዓመታት በኋላ በቀረበበት ክስ፣ የዘጠኝ ዓመታት እሥር ተፈርዶበታል። በእ.አ.አ 2017 ከእሥር የወጣው ሲምፕሰን፣ የስፖርት ማስታወሻዎቹ የራሱ እንደሆኑ ተናግሯል።
በቀድሞ ባለቤቱ ክስ ወቅት ጠበቃው የነበሩት ታዋቂው ጃኒ ካክረን፣ በሲምፕሰን ላይ በማስረጃነት የቀረበውን የእጅ ጓንት ፍ/ቤቱ ሲለካው መጥለቅ ባለመቻሉ፣ “ጓንቱ ልኩ ካልሆነ፣ ደንበኛዬን ልቀቁ” ማለታቸው፣ የፍርድ ሂደቱን የተከታተሉ ሁሉ የሚያስታውሱት ነው።