በአውሮፓ ሀገሮች በጥብቅ ከሚፈለጉ ቀንደኛ ሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች አንዱ ኢራቅ ውስጥ ተያዘ

  • ቪኦኤ ዜና
ፎቶ ፋይል- ፍልሰተኞች በትናንሽ ጀልባዎች የእንግሊዝን ቻናል እያቋረጡ

ፎቶ ፋይል- ፍልሰተኞች በትናንሽ ጀልባዎች የእንግሊዝን ቻናል እያቋረጡ

በአውሮፓ ሀገሮች በጥብቅ ከሚፈለጉ አደገኛ ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች አንዱ ትናንት ሰኞ ሰሜናዊ ኢራቅ ከፊል ራስ ገዟ ኩርዲስታን ውስጥ መያዙን የአካባቢው የጸጥታ ባለስልጣናት አስታወቁ።

የክልሉ የጸጥታ ተቋም ባወጣው መግለጫ "ጊንጡ" በሚል ቅጽል ስም የሚታወቀውን ባርዛን መጂድን ከዓለም አቀፉ ፖሊስ - ኢንተርፖል - በቀረበልን ጥያቄ እና ከተቋሙ የስለላ መረጃ ካገኝን በኋላ ሱሌይማንያ አካባቢ ይዘነዋል" ብሏል። ለክልሉ የፍትህ ሚኒስቴር ማስረከቡንም የጸጥታ ተቋሙ ጨምሮ አመልክቷል።

የብሪታኒያ ብሔራዊ የወንጀል ጉዳዮች ቢሮ በኤክስ ገፁ ላይ የባርዛን ማጂድን መታሰር ይፋ አድርጓል። ማጂድ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2022 ብሪታኒያ እና ቢልጂየም በጋራ ባካሂዱት ምርመራ በቤልጂየም ፍርድ ቤት በሌለበት በህገ ወጥ የሰው ዝውውር ወንጀል የጥፋተኝነት ውሳኔ የተሰጠው ሲሆን፤ ይህንኑ ተከትሎ ብሪታኒያ ሰውየውን ለመያዝ ትብብር እንዲደረግ ተማጽኖ አቅርባ ነበር።

ባርዛን ማጂድ 100 ፍልሰተኞን በአነስተኛ ጀልባዎች እና የጭነት ተሽከርካሪዎች እያሳፈረ በድብቅ ወደ ብሪታኒያ ለማስገባት ሞክሮ እንደነበር የብሪታኒያው የብሄራዊ ወንጀል ጉዳዮች ተቋም አመልክቷል።