ከኢትዮጵያ ጦር ጎን ተሰልፈው ከትግራይ ተዋጊዎች ጋር የተፋለሙት የአማራ ክልል ልይ ኃይሎች በኅዳር ወር በተደረሰው የሰላም ሥምምነት መሰረት ከሰሜን ትግራይ ለቀው መውጣታቸውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አስታወቀ።
መከላከያ ሰራዊቱ ዛሬ ሐሙስ ባወጣው መግለጫ የአማራ ክልል ኃይሎች ከሽሬ እና በአካባቢው ከሚገኙ ከተሞች ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸውን ያስታወቀ ሲሆን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ የክልሉ ኃይል ሲወጣ መመልከታቸውን ተናግረዋል። ሆኖም ከትግራይ ባለሥልጣናት እስካሁን የተሰጠ አስተያየት የለም።
Your browser doesn’t support HTML5
የአማራ ልዩ ኃይሎች እንደ ኤርትራ ሁሉ በኅዳር ወር የተፈረመው የሰላም ሥምምነት አካል ባለመሆናቸው ለሰላም ሥምምነቱ አተገባበር ላይ ትልቅ ፈተና ሆነው መቆየታቸው ሲነገር ቆይቷል።
በአክሱምና ሽሬ መካከል በምትገኘው ሰለኽለኻ በተባለች አካባቢ እንደሚኖሩ በስልክ የገለፁልን አንድ ስማቸው እንዲጠቅ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ ከአራት ቀናት በፊት ቁጥራቸው የበዛ አውቶብሶች የታጠቁ ኃይሎች ይዘው ከከተማው ሲወጡ መመልከታቸውን ገልፀውልናል።
ስምምነቱን የሚከታተለውን የአፍሪካ ኅብረት ማግኘት ባለመቻሉ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ስለመውጣቱ በገልተኛ አካልም ማረጋገጥ አልተቻለም።
የኤርትራ ኃይሎችም ከክልሉ ስለመውጣታቸው እስካሁን ግልፅ የሆነ መረጃ ባይኖርም የዐይን እማኞች የኤርትራ ኃይሎች ከሁለት የትግራይ ከተሞች ባለፈው ወር መውጣታቸውን አስታውቀው ነበር።