ከሜክሲኮ እስከ ዩናይትድ ስቴትስ ከዛም እስከ ካናዳ የሚሸፍን የፀሐይ ግርዶሽ ዛሬ ሰኞ መጋቢት 30፣ 2016 እንደሚከሰት በመጠበቅ ላይ ነው።
ሙሉ ግርዶሹ አራት ደቂቃ ተኩል ይቆያል በተባለው በዚህ ክስተት፣ ጨረቃ በፀሐይ እና በመሬት መካከል በመሆን ፀሐይን ሙሉ ለሙሉ ስለምትጋርድ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የቀን ጨለማ ይከሰታል።
የፀሐይ ግርዶሹ የሚሸፍነው ሕዝብ በብዛት የሚኖርባቸውን ክፍለ ግዛቶች በመሆኑ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ክስተቱን ለመታዘብ ወደ ሰማይ እንደሚያንጋጥጡ ይጠበቃል። ሙሉ ግርዶሽ በሚከሰትበት አካባቢ 44 ሚሊዮን ሰዎች ሲኖሩ፣ ክስተቱ በአጠቃላይ 200 ሚሊዮን ሰዎች የሚኖሩበትን አካባቢ ይሸፍናል። ሰዎች ወደ ሰማይ ሲያንጋጥጡ ለዓይናቸው ጥንቃቄ እንዲያደርጉና መነፅር እንዲጠቀሙ ባለሞያዎች መክረዋል።
በሰሜን አሜሪካ ሁሉም አካባቢ በሚባል ደረጃ ቢያንስ ከፊል ግርዶሽ እንደሚታይ፣ አንዳንድ ቦታዎች ግን ለ4 ደቂቃ ከ28 ሰከንድ ሙሉ ለሙሉ ግርዶሽ እንደሚከሰት ተነግሯል። ይህም ከሰባት ዓመታት በፊት በእ.አ.አ 2017 ከነበረው ግርዶሽ በእጥፍ የረዘመ ነው። ይህም ጨረቃ ለመሬት ይበልጥ በመቅረቧ ነው። በዚህ መጠን ቀጣዩ ግርዶሽ የሚከሰተው ከ21 ዓመታት በኋላ እንደሆነ ታውቋል።
ከሰላማዊ ውቅያኖስ አቅጣጫ የሚጀምረው ግርዶሽ ማዛልታን ከምትባል የሜክሲኮ ከተማ ተነስቶ፣ ከዛም ወደ ሰሜን አሜሪካ በማቅናት ቴክሳስ፣ ኦክላሆማ፣ አርካንሶ እንዲሁም ሌሎች 12 ግዛቶችን ከሸፈነ በኋላ ወደ ካናዳ በማቅናት፣ ኒውፋውንድላንድ የተሰኘችውንና አትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የምትገኘውን ግዛት በመሸፈን ይጠናቀቃል። ይህም በአጠቃላይ አምስት ሰዓታትን ይወስዳል።