ሚስጥራዊው በሽታ ምን እንደሆነ ማንም አያውቅም

  • ቪኦኤ ዜና

በደቡባዊቱ የህንድ ግዛት አንድሄራ ፕራዴሽ 500 ሰዎች ሆስፒታል ያስገባውና ለአንድ ሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነ ሚስጥራዊ በሽታ የጤና ባለሥልጣናቱን እና ባለሞያዎችን ግራ አጋብቷል።

የበሽታው መከሰት ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው በምታመርታቸው የእደ ጥበብ ሥራዎች ይበልጥ በምትታወቀው በጥንታዊቱ ከተማ ኢልሩ “ሰዎች ድንገት የሚያንቀጠቅጥ በሽታ ምልክት ማሳየት በጀመሩበት ወቅት ነው” ሲሉ የግዛቲቱ የሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ዳይሬክተር ጊታ ፕራሳዲኒ አስረድተዋል።

ከዚያን ጊዜ አንስቶም የታመሙት ሰዎች የማስመለስና የስሜት መናወጥ የህመም ምልክት፤ እንዲሁም አልፎ-አልፎ ራሳቸውን እስከመሳት ድረስ የታየባቸው መሆኑን 546 ሰዎች ወደ ሆስፒታል ገብተው መታከማቸው እና 148ቱ አሁንም በህክምና በመረዳት ላይ ሲሆኑ የተቀሩትም ሕክምና ተደርጎላቸው ወደ መኖሪያቤታቸው መላካቸውን የመንግስቱ ቃል አቀባይ ድሳሪ ናጋርጁና ተናግረዋል።

ከተለያዩ የሃገሪቱ ከፍተኛ የሳይንስ ተቋማት የተውጣጣ የባለ ምሞያዎች ቡድን ከአካባቢው ደርሶ የተለያዩ የምርመራ ሥራዎችን በማካሄድ ላይ መሆኑንም ተነግሯል።

ይሁንና "የዚህን ሚስጥራዊ በሽታ ምንነት እስካሁን ማንም አያውቅም።” ሲሉ የሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ዳይሬክተር ፕራሳዲኒ አረጋግጠዋል።