የኢትዮጵያ መንግሥት በአዲስ ዓመት ዋዜማ ከፈታቸው 757 እሥረኞች መካከል በሽብር ወንጀል ታሥረው የነበሩት የሙስሊም ማኅበረሰብ ጥያቄዎች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡
በፌደራል ማረሚያ ቤቶች፣ ቃሊቲ፣ ዝዋይ ድሬዳዋና ሸዋ ሮቢት እንዲሁም የፌደራል ማረሚያ ቤቶችን ሥራ በውክልና ከሚያከናውኑ ከደቡብና ከትግራይ ክልሎች እንዲሁም ሃረር ከሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ይቅርታ እንዲደረግላቸው ለይቅርታ ቦርድ ከቀረቡ 755 ታራሚዎች መካከል 720ዎቹ መሥፈርቱን በማሟላታቸው መፈታታቸው ታውቋል፡፡
የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጥያቄዎች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ከነበሩት መካከል ዘጠኙ የተፈቱት ከአራት ዓመታት እሥራት በኋላ ነው፡፡
የኮሚቴው አባላት የነበሩ አራት ሰዎች አሁንም እሥር ላይ ናቸው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የ“የሙስሊም ጉዳዮች” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ዩሱፍ ጌታቸው ከአራት ዓመታት እሥራት በኋላ ዛሬ በመለቀቁ መደሰቱን የገለፀው በእንግሊዝኛ ስሙ ምኅፃር ሲፒጄ በሚል የሚታወቀው የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋች ቡድን “ቀድሞም ቢሆን ዩሱፍ መታሠር አልነበረበትም” ብሏል፡፡
የሲፒጄ የአፍሪካ መርኃግብር አስተባባሪ አንጄላ ኲንታል ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ መንግሥት ሌሎቹንም “ሥራቸውን በማከናወናቸው ብቻ ያሠራቸውን” ጋዜጠኞች አሁኑኑ እንዲፈታ ጠይቀዋል፡፡
ፅዮን ግርማ ከጋዜጠኛ ዩሱፍ ጌታቸው ጋር ያደረገችውን ቃለ ምልልስ የያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡
Your browser doesn’t support HTML5