ከናያሜይ ኒዤር፣ የመጣ ነው የተባለ 1ሺሕ 400 ኪ.ግ. የሚመዝን ወርቅ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተይዟል፡፡
የወርቁን ከሶስት ሣምንታት በፊት መያዝ ተከትሎ፣ የኒዤር ፖሊሶች ምርመራ መጀመራቸውን ኤኤፍፒ ከፍትህ አካላት አገኘሁት ያለውን መረጃ ጠቅሶ ዘገቧል።
100 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ዋጋ እንደሚያወጣ የተገመተው ወርቅ አዲስ አበባ ላይ መያዙን ‘ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል’ የተሰኘው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ቀን ሳይጠቅስ ማስታወቁንም ዘገባው አመልክቷል።
የኒዤር የፍትሕ ሚኒስትር፣ አሊዮ ዳውዳ በመንግስታዊ ሬዲዮ ሲናገሩ፣ መሥሪያ ቤታቸው ጉዳዩን በተመለከተ ለፖሊስ ማስታወቁን እና ምርመራም በመካሄድ ላይ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ከእ.አ.አ 2004 ወዲህ የወርቅ ምርቷ እንደጨመረ የሚነገረው ኒዤር፣ አንድ ሺሕ የሚሆኑ ባህላዊ የወርቅ አውጪዎች በአገሪቱ ሰሜን እና ምዕራብ አካባቢ በተበታተነ ሁኔታ ይገኛሉ።
አካባቢዎቹ የፀጥታ ችግር ያለባቸውና የታጠቁ ጂሃዲስቶች እንደሚንቀሳቀሱበት ታውቋል።
ምርመራው የወርቁን መነሻ እና ላኪዎቹን ለመለየት የሚደረግ ሲሆን፣ ወርቁን በሕገ ወጥ መንገድ በማስተላለፍ የተሳተፉ ግለሰቦች ለፍርድ እንደሚቀርቡ የፍትሕ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ጉዳዩ በጀኔራል አብዱራህማኔ ቲያኒ የሚመራውን ሁንታ ያሳሰበው ጉዳይ መሆኑንም ሚኒስትሩ አክለው ገልፀዋል። በኢትዮጵያ የሚገኘውን ወርቅ ወደ ኒዤር የመመለስ ሂደት እንደሚጀመርም አስታውቀዋል።
የኒዤር ማዕድን ሚኒስትር፣ የማዕድን ማውጣት ፈቃድ እንዳይሰጥ ለግዜው ማገዱም ታውቋል። በኒያሜይ በሚገኘው ዲዮሪ ሃማኒ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚሠሩና በደርዘን የሚቆጠሩ የጉምሩክ ሠራተኞች፣ የፖሊስ እና ሌሎችም የፀጥታ አካላት ወደ ሌላ ቦታ መዛወራቸውን የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።