በናይጄሪያ ሶኮቶ ክፍለ ግዛት የተማሪዋ መገደል የቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ የሰዓት እላፊ ታወጀ

በናይጄሪያ ሶኮቶ ክፍለ ሀገር የኮሌጅ ተማሪዋ ዲቦራ ያኩቡ መገደሏን ተከትሎ የግድያው ተጠርጣሪዎች እንዲለቀቁ በመጠየቅ የቀጠለውን የተቃውሞ ሰልፍ ለማብረድ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ የሃያ አራት ሰዓት፣ የሰዓት እላፊ ታውጇል።

ተማሪዋን ነቢዩ መሀመድን የሚያንቋሽሽ መልዕክት በማኅበራዊ መገናኛ ዋትስአፕ አማካይነት አጋርታለች ተብላ ባለፈው ሀሙስ ተማሪዎች በድንጋይ ደብድበው ከገደሏት በኋላ አስከሬኗን አቃጥለውታል።

ቅዳሜ የታወጀው የሰዓት እላፊ ተከትሎ ትናንት ዕሁድ መንገዶች ጭር ብለው የዋሉ ሲሆን አብያተ ክርስቲያን እና መስጊዶችም ተዘግተዋል።

ከተማሪዋ መገደል በተያያዘ ፖሊስ አርብ ያሰራቸውን ሁለት ተማሪዎች እንዲለቅቅ ቅዳሜ ዕለት በብዙ መቶዎች የተቆጠሩ ነዋሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ ያካሄዱ ሲሆን ሁለት የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያን ላይ ጥቃት አድርሰዋል። መኪናዎች እና መደብሮች ላይ ጉዳት ያደረሱ ሲሆን ፖሊሶች አስለቃሽ ጋዝ ረጭተው በትነዋቸዋል።

የሼሁ ሻጋሪ ኮሌጅ ተማሪዋ መገደል አምነስቲ ኢንተርናሲናልን ጨምሮ ብዛት ያላቸው የመብት ቡድኖች እና ሃይማኖታዊ ተቁዋማት ነቅፈዋል።

የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ግድያውን አጥብቀው ያወገዙ ሲሆን ነጻ ምርመራ እንዲካሄድ ጠይቀዋል።

የጸጥታ ቡድኖች በበርካታ የናይጄሪያ ሰሜናዊ ክፍለ ገዛቶች ሁከት ሊቀጣጠል ይችላል ብለው አስጠንቅቀዋል። ከሶኮታ በጣም በምትርቀው በካዱና ክፍለ ሃገር ይህንኑ ለመከላከል ቅዳሜ ዕለት ባለሥልጣናቱ ከሃይማኖታዊ ጉዳዮች የተያያዙ የተቃውሞ ሰልፎች ከልክለዋል።