የናይጄሪያ ሠራተኞች በኑሮ ውድነቱ ቀውስ የሥራ ማቆም አድማ ጀመሩ

ፋይል፡ የካቲት 19 2016 በአቡጃ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ አንድ ሰልፈኛ የናይጄሪያ የሠራተኛ ምክር ቤት (NLC) ባንዲራ ሲያውለበልብ፡፡

የናይጄሪያ ሠራተኛ ማህበራት ከዛሬ ሰኞ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ የሥራ ማቆም አድማ ጀመሩ፡፡

ማህበራቱ አድማውን የጀመሩት ከመንግስት ጋር ያደረጉት ዝቅተኛው የደመወዝ ወለል ድርድር ከከሸፈ በኋላ ነው፡፡

በአድማው መሠረት በዛሬው ዕለት ትምህርት ቤቶች፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ አየር ማረፊያዎች እና ብሄራዊ የመብራት ሃይል አውታሮች ተዘግተዋል።

በናይጄሪያ ያለው የኑሮ ውድነት ችግር ለብዙዎች የምግብ አቅርቦት ማግኘትን አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡

ዋነኛው የናይጄሪያ የሠራተኛ ምክር ቤት (NLC) እና የንግድ ማህበራት ህብረት ምክር ቤት (TUC) መንግሥት ዝቅተኛውን የ60,000 ናራ (45 ዶላር) የደመወዝ ጭማሪ ከፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

ማህበራቱ መንግሥት ጥያቄያቸውን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሠራተኞች የሥራ መሳሪያዎቻቸውን ሁሉ እንዲያስቀምጡ አሳስበዋል ፡፡

ማህበራቱ ባወጡት የጋራ መግለጫ ከረሀብ የማይከላከል ነው ያሉትን ዝቅተኛ ደመወዝ በመቃወም ከቤት እንደማይወጡ አስታውቀዋል፡፡

የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ቦላ አህመድ ቲኒቡ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ የነዳጅ ድጎማ እና የገንዘብ ቁጥጥርን በማቆማቸው፣ የቤንዚን ዋጋ በሶስት እጥፍ እንዲጨምር እና የኑሮ ውድነት እንዲባባስ አድርገዋል፡፡ የሀገሪቱ ገንዘብ የኒያራ ዋጋም ከዶላር ጋር ሲወዳደር ቀንሷል፡፡

ፕሬዚዳንት ቲኒቡ የተደረጉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ተጨማሪ የውጭ መዋዕለ ንዋይን ሊስቡ ስለሚችሉ ህዝቡ በትዕግሥት እንዲጠባበቅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡