በናይጄሪያ ግጭት 55 ሰዎች ሕይወታቸውን አጡ

በሰሜን ማዕከላዊ ናይጄሪያ በሙስሊም ከብት አርቢዎች እና በክርስቲያን ገበሬዎች መካከል በፈነዳ ግጭት 55 ሰዎች መገደላቸውን ቀይ መስቀል እና የማሕበረሰብ መሪዎች ማስታወቃቸውን የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።

ማንጉ በተባለው አውራጃ የሰዓት እላፊ ቢታወጅም፣ ት/ቤቶችና የሃይማኖት ተቋማት መቃጠላቸውና መዘረፋቸው ታውቋል።

በአብዛኛው ክርስቲያኖች የሚገኙበት የሙዋጋቩል ጎሳ ልማት ማሕበር፣ ከፉላኒ ወገን ያሉትን ሙስሊም ከብት አርቢዎች ለጥቃቱ እና ለ30 ሰዎች ሞት ተጠያቂ አድርገዋል።

የሙስሊም ድርጅት ተወካዮች በበኩላቸው 25 አስከሬኖችን ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።

ኤኤፍፒ ተመልክቼዋለሁ ባለው የናይጄሪያ ቀይ መስቀል ማኅበር ሪፖርት መሠረት፣ 55 ሰዎች መገደላቸው እና ከ100 በላይ የሚሆኑ ደግሞ መጎዳታቸው ታውቋል።

1ሺሕ 500 የሚሆኑ ሰዎች መፈናቀላቸው ሲታወቅ፣ በሁለት ካምፖች እንዲጠለሉ ተደርጓል ተብሏል።

ባለፈው ገና በደረሰ ጥቃት 200 ክርስቲያኖች ከተገደሉ ወዲህ፣ በአካባባው ውጥረት መስፈኑ ተነግሯል።