የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ የዩናይትድ ስቴትሱን አቻቸውን ዶናልድ ትረምፕን ለማግኘት የመጀመሪያው የጥቁር አፍሪካ ሃገር መሪ ሆነዋል።
ሁለቱ መሪዎች በዛሬ የዋይት ሃውስ ቤተመንግሥት ስብሰባቸው ወቅት የሽብር ፈጠራን ሥጋትና በሕዝቧ ብዛት በ200 ሚሊየን ሰዋ ከአፍሪካ ቀዳሚ በሆነችው ናይጀሪያ ምጣኔኃብት ጉዳይ ላይ ይወያያሉ።
የናይጀሪያ ጦር ቦኮ ሃራምና እሥላማዊ መንግሥት በሚባሉት የሽብርና የሁከት ቡድኖች ላይ የሚያካሂደውን ዘመቻ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ በተደራጁ ጄቶችና በመሣሪያ ለመደገፍ፣ እንዲሁም በአደንዛዥ ዕፅዋትና ቅመማቅመም፣ በጦር መሣሪያና በሕገወጥ የሰዎች ሽግግርና ዝውውር ላይ የሚደረገውን ቅኝት ለማጠናከር የትረምፕ አስተዳደር ባለፈው ዓመት የ6 መቶ ሚሊየን ዶላር እርዳታ አፅድቆ ነበር።
በሁለቱ ሃገሮች መካከል የነበረው ተመሣሣይ የመደጋገፍ ንግግር የቀደመው የኦባማ አስተዳደር ይገልፃቸው በነበሩ ከሰብዓዊ መብቶች ረገጣዎች ጋር የተያያዙ ሥጋቶች ምክንያት ተደናቅፎና ቆሞ እንደነበር ተገልጿል።
ፕሬዚዳንት ቡሃሪ ከፊታቸው ለተደቀነው ምርጫ እንደገና ለመቅረብና ለማሸነፍ ባለፈው የምረጡኝ ቅስቀሳቸው ወቅት ቦኮ ሃራምን እንደሚያጠፉ የገቡትን ቃል ለመጠበቅ የዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው እየተነገረ ነው።