አቶ ታየ ደንድኣ፣ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ባጋሩት ጽሑፍ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ከሰላም ሚኒስቴር የሚኒስትር ዴኤታ ሓላፊነታቸው እንዳነሧቸው፣ ደብዳቤውን በአስረጅነት በማያያዝ አስታውቀዋል፡፡
ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ርምጃ፣ አቶ ታየ ክፉኛ ነቅፈዋል፡፡
“ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ” በሚል ርእስ ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድን ተችተዋል፡፡
“እውነት መስሎኝ፣ በሀገር ህልውና ስም ሲያካሒዱ የነበረውንና ኢትዮጵያውያንን ከማገዳደል አልፎ አገሪቷን ያዳቀቃትን ከንቱ ጦርነት ሳዳምቅልዎ በነበረበት ወቅት ሲያወድሱኝ ነበር፤” ያሉት አቶ ታዬ፣ “ዛሬ ነገሩ ገብቶኝ፣ የወንድማማቾች መገዳደል ይቆም ዘንድ ለሰላም በመወገኔ ከሥልጣን አነሡኝ፤” ሲሉም የተሰናበቱበትን ምክንያት ገልጸዋል፡፡
አቶ ታየ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጻፈላቸውን ደብዳቤ አያይዘው ይህን ቢሉም፣ እስከ አኹን፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤትም ኾነ ከሌላ የመንግሥት አካል፣ በጉዳዩ ላይ የተባለ ነገር የለም፡፡ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለማግኘት ሙከራ እያደረግን ነው ምላሽ ስናገኝ በሌላ ዘገባ እንመለሳለን።
አቶ ታየ ያጋሩት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተፈረመው ደብዳቤ፣ “ከመስከረም 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ኾነው ላበረከቱት አስተዋፅኦ እያመስገንኹ፣ ከታኅሣሥ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከሓላፊነት የተነሡ መኾኑን አስታውቃለኹ፡፡” የሚል ነው፡፡
አቶ ታየ በሓላፊነት ቦታ ላይ እያሉም፣ በከፍተኛ አመራርነት ያሉበትን መንግሥት በተደጋጋሚ በመተቸት ይታወቃሉ፡፡
በቅርቡ እንኳን፣ “ጦርነት ይቁም፤ ሰላም ይስፈን” በሚል የተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ መከልከሉን አስመልክቶ፣ “የጦርነት ከበሮ በመታንበት አደባባይ፣ ዜጎች በሰላማዊ ሰልፍ ጦርነትን እንዳይቃወሙ መከልከል መጥፎ ትርጉም ይሰጣል፤” ሲሉ፣ ልዩነታቸውን በገሃድ መግለጻቸው ይታወቃል፡፡