ኒው ዜላንድ ውስጥ ባለፈው ሰኞ በተከሰተው እሳተ-ጎመራ ምክንያት የሞቱት ስምንት ሰዎች አስካሬኖችን ለማንሳት፣ ነገ ዋይት ደሴት ወደ ተባለው ቦታ ሰራተኞች እንደሚልኩ ባለሥልጣኖች ተናግረዋል።
ዋሺንግተን ዲሲ —
የእሳተ-ጎመራው ፍንዳታ ባለመረጋጋቱ፣ አስከሬኖችን የሚያነሱ ሰራተኞች የመላኩን ጉዳይ ባለሥልጣኖቹ አዘግይተውት ነበር። ሌላ ከባድ እሳተ ጎመራ ሊነሳ የሚችልበት 40 እና 60 ከመቶ ዕድል መኖሩን፣ የኒው ዚላንድ የርዕደ-መሬት ቁጥጥር አገልግሎት አስታውቋል። እሳተ - ጎመራው ከተነሳበት ቦታ መርዛማ ጋዝ መውጣቱ ቀጥሏል። ደሴቱ በአሲድ አመድ የተሸፈነ መሆኑ ታውቋል።
የሞቱት ሰዎች ብዛት ዛሬ 8 የደረሰው፣ ሁለት ከአደጋው ተርፈው ሆስፒታል የገቡ ሰዎች በመሞታቸው ነው። ቢያንስ 27 ሰዎች ከአካላቸው 71 ከመቶ በላይ ቃጣሎ ደርሶባቸዋል። 22 ደግሞ ከባድ ቃጠሎ ገጥሟቸዋል። ሰለባ ለሆኑት ሰዎች ህክምና ለማድረግ፣ ተጨማሪ 1.2 ሚልዮን አጸፋ ሴንቲ ሜትር ቆዳ እንደያስፈልግ፣ የጤና ጥበቃ ባለሥልጣኖች ተናግረዋል።