በኒው ዮርክ ከተማ ባቡር ውስጥ ግለሰቧን በእሳት ለኩሶ በመግደል የተጠረጠረው ተያዘ

በኒው ዮርክ ከተማ ባቡር ውስጥ አንዲትን ሴት ልብሷን በእሳት ለኩሶ በቃጠሎው ሕይወቷ እንዲያልፍ አድርጓል የተባለ ተጠርጣሪ

በኒው ዮርክ ከተማ ባቡር ውስጥ አንዲትን ሴት ልብሷን በእሳት ለኩሶ በቃጠሎው ሕይወቷ እንዲያልፍ አድርጓል የተባለ ተጠርጣሪ ወዲያውኑ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ታውቋል። የጥቃቱ ሰለባ የሆነችው ግለሰብ በወቅቱ ምናልባትም እንቅልፍ ሳይዛት አልቀረም ተብሏል።

በደኅንነት ካሜራ እና ፖሊሶች ላያቸው ላይ አድርገው በሚዞሩት ካሜራ አማካይነት የተገኘውን ምስል የተመለከቱ ሦስት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በሰጡት ጥቆማ መሠረት ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ታውቋል።

ተጠርጣሪው የሟቿን ልብስ ምናልባትም እሳት መለኮሻ ላይተር ሳይሆን አይቀርም ባሉት ነገር ሲለኩስ የባቡሩ ካሜራ እንደቀረጸው የኒው ዮርክ ፖሊስ ኮሚሽነር ጀሲካ ቲሽ እስታውቀዋል። “የኒው ዮርክ ሰዎች በድጋሚ ትብብራቸውን አሳዩ” ያሉት ኮሚሽነሯ “ድርጊቱ አንድ ሰው በሌላው ላይ ሊፈጽመው የሚከብድ አሳዛኝ ወንጀል ነው” ሲሉም ገልፀውታል።

ፖሊስ ተጠርጣሪውና ሟቿ ይተዋወቃሉ ብሎ እንደማያምን አስታውቋል። ግለሰቡ ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ ከባቡሩ በመውጣት በዛው ጣቢያ ውስጥ ከባቡሩ አቅራቢያው ባለ አግዳሚ ወንበር ላይ ተቀምጦ እንደነበረ ግለሰቧን ለመርዳት የሚመላለሱት ፖሊሶች ላያቸው ላይ አድርገውት በሚዞሩት ካሜራ በግልጽ በመቀረጹና፣ ፎቶ ግራፉም ለሕዝብ በመሰራጨቱ ይህንንም ሰዎች ለይተው ለፖሊስ በማሳወቃቸው በሚቀጥለው የባቡር ጣቢያ ሊያዝ ችሏል።