የየመን ተፋላሚ አንጃዎች ለአራት ዓመታት የዘለቀውን የርስ በርስ ጦርነት ለማብቃት በታቀደው አዲስ ዙር የሰላም ሥምምነት ለመካፈል ስዊድን ይገኛሉ። ጦርነቱ ያቺን አነስተኛ የዓረብ ሠላጤ ሃገር ወደ ረሃብ አፋፍ እየገፋት ነው ተብሏል።
ሪምቦ ስዊድን ዛሬ የተጀመረውን የሰላም ንግግር ያደራጀው የተባበሩት መንግሥታት ሲሆን፣ በሳዑዲ በሚደገፈው መንግሥትና በኢራን በሚታገዙ የሁቲ አማጽያን መካከል ድርድር ሲደረግ ከሁለት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው።
አዲሱ የሰላም ንግግር የሚደረገውም፣ እጅግ አስከፊ እየሆነ የመጣው የሰብዓዊ ቀውስ ዓለምቀፉን ኅብረተሠብ በእጅጉ ባሳሰበበትና የጋዜጠኛ ጃማል ካሾጊ ኢስታንቡል በሚገኘው የሳዑዲ ቆንሲላ ጽሕፈት ቤት ውስጥ መገደል ባስጣቆጣው ወቅት ነው።
ጽሕፈት ቤቱን በዋሺንግተን ያደረገው የመካከለኛው ምሥራቅ ተቋም ምሁር ዙቤር ዑክባል ለአሜሪካ ድምፅ ሲናገሩ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እንደገና ወደ ሰላም ድርድሩ ተመልሳ እንድትመጣ የገፋት፣ በካሾጊ መገደል የተቆጡ የዩናይትድ ስቴትስ የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት አባላት፣ ለሪያድ የሚሰጠው ዕርዳታ እንዲቆረጥ ጥረት መያዛቸው ነው ብለዋል።
በሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች መካከል የተባበሩት መንግሥታትን ወክለው የሚደራደሩት ማርቲን ግሪፊዝ በበኩላቸው ሲያስረዱ፣ የአጀንዳው ዓብይ ጉዳዮች፡ የሰንዓን ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መቆጣጠር የሰብዓዊ ዕርዳታዎች ያለችግር ማለፍ የሚችሉበት መንገድና የሥልጣን መጋራት ሥምምነት ጥያቄ ናቸው ብለዋል።
ሁለቱ የየመን ተፋላሚ አንጃዎች፣ ቀደም ሲል ምርኮኞችን ለመለዋወጥ ከሥምምነት የደረሱ ቢሆንም፣ ታዛቢዎች በዛሬው ድርድር አዲስ ግኝት ሊፈጠር ይችላል የሚለውን ተስፋ ማጋነን አይፈልጉም።