አስቸኳይ ርዳታ ካልተደረገ፣ በጦርነት በደቀቀችው ሱዳን 230 ሺሕ የሚሆኑ ሕፃናትና አራሶች በረሃብ ሊሞቱ ይችላሉ ሲል የተመድ የሕፃናት አድን ድርጅት አስታውቋል።
አስራ አንድ ወራት ባስቆጠረውና በሁለት ተቀናቃኝ ጀኔራሎች መካከል በሚካሄደው ጦርነት ሳቢያ፣ በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ተፈናቅለዋል።
የቦምብ ድብደባው ፣ የእርሻ ማሳዎችና ፋብሪካዎች ውድመት ሱዳንን በዓለም ላይ ካሉ አስከፊ የምግብ ቀውስ ውስጥ ከሚገኙ ሀገራት እንድትመድ እንዳደረጋት በሱዳን የሕፃናት አድን ድርጅቱ ዲሬክተር አሪፍ ኑር ተናግረዋል።
“230ሺሕ የሚሆኑ ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡር ሴቶች እና አራሶች በመጪዎቹ ወራት ሕይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ” ሲል የእንግሊዙ የሕፃናት አድን ድርጀት ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል።
#Ramadan looks very different this year in #Sudan222,000 severely malnourished children & more than 7,000 new mothers are likely to die from hunger without critical action."We%27re seeing massive hunger, suffering & death. And yet the world looks away", Dr Arif Noor @SC_inSudan pic.twitter.com/MDZuJq3Ter
— Save the Children International (@save_children) March 13, 2024
በሱዳን ከ2.9 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ለአስከፊ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መጋለጣቸውን እና 729ሺሕ የሚሆኑና ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ደግሞ ለአደገኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መዳረጋቸውን በጎ አድራጊ ድርጀቱ ጨምሮ አስታውቋል።
በሱዳን የሚካሄደው ጦርነት በዓለም ትልቁን የረሃብ ቀውስ ሊቀሰቅስ ይችላል ሲል የዓለም የምግብ ፕሮግራም በቅርቡ አስጠንቅቋል።