የዚምባብዌ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤና ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ ያለመከሰስ ከለላ ተሰጣቸው።
አንድ የገዥው ዛኑ-ፒኤፍ ፓርቲ ባለሥልጣንና ዋና ከተማዪቱ ሃራሬ ውስጥ የሚገኝ ጋዜጠኛ ለቪኦኤ የዚምባብዌ አገልግሎት ዛሬ እንዳረጋገጡት ሙጋቤ ጡረታቸውን በተመለከተ ሥልጣናቸውን በግድ እንዲለቅቁ ካደረጓቸው የሃገሪቱ ጄነራሎችና ከፖለቲካ መሪዎች ጋር እየተደራደሩ ናቸው።
ሙጋቤ በሥልጣን ዘመናቸው ምርጫዎችን ያጭበረብሩ እንደነበረ፣ ሙስናና እንዲንሠራፋ መፍቀዳቸውን፣ በሃገሪቱ ውስጥ በሺሆች በሚቆጠሩ የፖለቲካ ባላንጦቻቸውና ተቃውሚዎች ላይ ለተካሄዱ የሥቃይ አያያዞችና ግድያዎች ተጠያቂ መሆናቸውን በመግለፅ የመብቶች ተሟጋች ቡድኖች ክሦችን ሲያሰሙ ቆይተዋል።
ሮበርት ሙጋቤ ፕሬዚዳንት በነበሩ ጊዜ ወጣቷን ባለቤታቸውን ግሬስ ሙጋቤን በቦታው ለማስቀመጥ በማሰብ ባለፈው ጥቅምት 25 ከሥልጣናቸው አባርረዋቸው የነበሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ኤመርሰን ምናንጋግዋ ለሁለት ሣምንታት ያህል ዘወር ብለው ከቆዩባት ደቡብ አፍሪካ ተመልሰው ሃራሬ የገቡ ሲሆን ነገ፣ ዓርብ ቃለ-መሃላ ፈፅመው አዲሱ የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት እንደሚሆኑ የፓርላማው አፈ-ጉባዔ አስታውቀዋል።
ዚምባብዌ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ እንድታካሂድ የዩናየትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርሰን አዲሶቹን መሪዎች አሳስበዋል።