ድንበር የለሽ ሃኪሞች ቡድን ትግራይ ውስጥ ስለተገደሉት ባልደረቦቹ የኢትዮጵያ መንግሥት መልስ እንዲሰጥ ጠየቀ

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል፦ ድንበር የለሽ ሃኪሞች ቡድን ሎጎ

ድንበር የለሽ ሃኪሞች ቡድን ትናንት ሐሙስ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ የተገደሉትን ባልደረቦቹን በተመለከተ ኒው ዮርክ ታይምስ በሰኔ 2013 ዓ.ም ያወጣውን የምርመራ ሪፖርት አስታውሷል።

ባልደረቦቹ ማሪያ ሄርናንዴዝ፣ ቴድሮስ ገብረ ማርያም እና ዮሃንስ ሃለፎም በተመለከተ ጋዜጣው ይፋ ባደረገው የክትትል ሪፖርት ለግድያው ተጠያቂው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መሆኑን ገልፆ አንድ የሰራዊቱ አዛዥ በቀጥታ ተሳትፈዋል ማለቱን የቡድኑ መግለጫ አስታውሷል።

የድንበር የለሽ ሃኪሞች ስፔይን ፕሬዝዳንት ፖላ ጊል፤ "የኢትዮጵያ መንግሥት በባልደረቦቻችን ላይ ሆን ተብሎ የተፈጸመው ግድያ ተጠያቂዎቹ የመከላከያ ኃይሉ አባላት እንደሆኑ ለሚገልጸው የኒው ዮርክ ታይምስ ሪፖርት መልስ እንዲሰጥ እንጠይቃለን" ብለዋል።

ኤም.ኤስ.ኤፍ ባልደረቦቹ ላይ ከተፈጸመው አሳዛኝ ግድያ ጀምሮ ግድያውን አስመልክቶ ሙሉ መረጃ ለማግኘት እና ተጠያቂዎችም ኃላፊነት እንዲወስዱ ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ፖላ ጊል በመግለጫው ላይ ጠቁመዋል።

"መሥሪያ ቤታችን በራሱ በኩል ያደረገው እና ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ያጋራው የክትትላችን ውጤት የግድያውን ተጠያቂዎችም ሆነ ለምን እንደገደሏቸው በርግጠኝነት ለማወቅ አልቻለም" ብለዋል።

አያይዘውም "ግድያው በተፈፀበት ወቅት በአካባቢው የነበሩትን ሁለቱንም ወገኖች የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይሎች እና የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባርን በግድያው ተሳትፈው እንደሆነ በይፋም በሁለትዮሽ መስመርም ጠይቀናል። በጉዳዩ ዙሪያ ያደረጓቸውን ክትትሎች እና ግምገማዎች ውጤትም እንዲያጋሩን ጠይቀናል" ያሉት የድንበር የለሽ ሀኪሞች ቡድኑ ባለሥልጣን እስካሁን ስለግድያው ሁኔታ የተሰጣቸው ማብራሪያም ሆነ በተጠያቂነት ኃላፊነቱን የወሰደ አካል እንደሌለ ገልፀዋል።

"የኢትዮጵያ መንግሥት በጉዳዩ ዙሪያ ምርመራውን መቀጠሉን እናውቃለን ውጤቱን ባፋጣኝ ሊሳውቀን ይገባል" ብለዋል።